ሕክምናHikimna · Amharic health reference
በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው። Written by an MD. Educational only.

እማዬና አባዬ ከኢትዮጵያ ሲመጡ፦ ከመምጣታቸው በፊት የሚዘጋጁ አምስት ነገሮች

Parents visiting from Ethiopia: five things to prepare before they come

በሐኪም (MD) የተጻፈ · Written by an MD · 2026-09-27

ምንድን ነው?

ቪዛው መጣ፣ ቲኬቱ ተቆረጠ፣ እማዬና አባዬ ከኢትዮጵያ ሊመጡ ነው። ለብዙ ቤተሰቦች ይህ ትልቅ ደስታ ነው፤ ለልጅ መወለድ፣ ለሠርግ ወይም ለረጅም ቆይታ። ግን ብዙ ቤተሰቦች ዘግይተው የሚማሩት አንድ ነገር አለ። እዚህ አሜሪካ፣ አንድ ቀን ሆስፒታል መተኛት ብቻ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ሊያስከፍል ይችላል።

ብዙ ወላጆች በስልሳዎቹና በሰባዎቹ ዕድሜ ላይ ናቸው። ብዙዎቹ ደም ግፊት (high blood pressure) ወይም ስኳር (diabetes) አለባቸው። ረጅሙ ጉዞ፣ አዲሱ ምግብ፣ ብርዱና አዲሱ ቤት ደግሞ ሰውነታቸውን ይፈትናሉ። ስለዚህ ከመምጣታቸው በፊት አምስት ነገሮችን እናዘጋጅ።

አደገኛ ምልክቶች

ከደረሱ በኋላ፣ በተለይ ከረጅሙ ጉዞ በኋላ ባሉት ሳምንታት፦

  • አንድ እግር ብቻ ካበጠ፣ ካመመ፣ ከሞቀ ወይም ቀለሙ ከተቀየረ፣ በዚያው ቀን ሐኪም ያግኙ። ይህ የእግር ክሎት (DVT) ምልክት ሊሆን ይችላል።
  • ድንገት ትንፋሽ ካጠራቸው፣ በጥልቀት ሲተነፍሱ የሚብስ የደረት ሕመም ካለ፣ ልባቸው በፍጥነት ቢመታ ወይም ራሳቸውን ቢስቱ፣ ፈጽሞ ችላ አይበሉ። 911 ይደውሉ።
አምስቱ ዝግጅቶች
  • አንደኛ፣ ከጉዞው በፊት ቼካፕ (checkup)። እዛው ኢትዮጵያ እያሉ ሐኪማቸውን ያግኙ። ደም ግፊታቸውና ስኳራቸው ኮንትሮል መሆኑን ያረጋግጡ። እዚህ መጥቶ ማስተካከል ብዙ ገንዘብና ጊዜ ይወስዳል። የቅርብ ጊዜ የላቦራቶሪ ውጤታቸውንም ኮፒ ይዘው ይምጡ።
  • ሁለተኛ፣ መድኃኒታቸው። የሚወስዱትን ኪኒን ሁሉ በራሱ ማሸጊያ ይዘው ይምጡ፤ ለቆይታቸው በቂ ይሁን። በኤርፖርት ሲገቡ መድኃኒቱን ያሳውቁ (declare)። ከሐኪማቸው የመድኃኒቱን ስምና መጠኑን የሚያሳይ ሊስት ያጻፉ። የኢትዮጵያ ፕሪስክሪፕሽንን (prescription) እዚህ ያሉ ፋርማሲዎች አይቀበሉም፤ መድኃኒቱ ካለቀ እዚህ ያለ ሐኪም ያንን ሊስት አይቶ ነው የሚያዝላቸው።
  • ሦስተኛ፣ ቪዚተር ኢንሹራንስ (visitor insurance)። ከጉዞው ቀን ጀምሮ እንዲሰራ ቀድመው ይግዙ። ብዙ ፕላኖች ቀድሞ ያለባቸውን በሽታ፣ እንደ ደም ግፊት ወይም ስኳር፣ አይሸፍኑም። ስለዚህ አኪዩት ኦንሴት (acute onset of pre-existing condition) የሚል ከቨሬጅ ያለውን ይፈልጉ። ይህ ማለት ያ የቆየ በሽታ በድንገት ኢመርጀንሲ ቢፈጥር የሚሸፍን ማለት ነው። ከሰባ ዓመት በላይ ከሆኑ አማራጩ ስለሚያንስ ቀደም ብለው ይፈልጉ። ሁኔታዎቹ ከፕላን ፕላን ይለያያሉ፤ ከመግዛትዎ በፊት ዝርዝሩን ያንብቡ።
  • አራተኛ፣ የአውሮፕላኑ ጉዞ። ረጅም ሰዓት ሳይንቀሳቀሱ ሲቀመጡ በእግር ቬይን (vein) ውስጥ ደም ቀስ ብሎ ይሄዳል፤ ቀስ ብሎ የሚሄድ ደም ደግሞ ክሎት (blood clot) ሊሰራ ይችላል። ዕድሜ ሲጨምር ይህ ሪስክ ከፍ ይላል። በየአንድ ወይም ሁለት ሰዓቱ ተነስተው እንዲራመዱ ይምከሯቸው፤ ተቀምጠውም እግራቸውን ወደላይ ወደታች ያንቀሳቅሱ፤ ውሃ ይጠጡ።
  • አምስተኛ፣ እዚህ ከደረሱ በኋላ ያለው ኑሮ። የሰዓት ልዩነት፣ ምግብና እንቅስቃሴ፣ ብርድ፣ አዲሱ ቤትና ብቸኝነት። ዝርዝሩ ከታች አለ።
እዚህ ከደረሱ በኋላ
  • የሰዓት ልዩነት፦ ኢትዮጵያ ሌሊት ሲሆን እዚህ ቀን ነው። መድኃኒታቸውን መቼ እንደሚወስዱ በሊስቱ ላይ በአዲሱ ሰዓት ይጻፉላቸው። ኢንሱሊን (insulin) የሚወስዱ ከሆነ ከመጓዛቸው በፊት ሐኪማቸውን ይጠይቁ።
  • ምግብና እንቅስቃሴ፦ እዛ ብዙ በእግር ይራመዱ ነበር። እዚህ ግን በመኪና ነው፣ ቤት ውስጥ ይቀመጣሉ፣ ምግቡም ይበዛል። ይህ ስኳርና ደም ግፊትን ከፍ ያደርጋል። በየቀኑ አብረው ይራመዱ።
  • ብርዱ፦ ብርድ ሲመታ የደም ስሮች ጠባብ ይሆናሉ፤ ደም ግፊት ይጨምራል፣ ልብም የበለጠ ይደክማል። ሞቅ ያለ ልብስ ያዘጋጁላቸው።
  • የፍሉ ክትባት (flu shot)፦ ክረምት ከመግባቱ በፊት እንዲወስዱ ያድርጉ። ብዙ ፋርማሲዎች ያለ ቀጠሮ ይሰጡታል። ዕድሜያቸው ከስልሳ አምስት በላይ ከሆነ ለእነሱ የተዘጋጀ ጠንከር ያለ ክትባት አለ፤ ፋርማሲስቱን ይጠይቁ።
  • አዲሱ ቤት፦ ደረጃ፣ የሚያንሸራትት ባዝታብ (bathtub)፣ ሌሊት ጨለማ። ለመውደቅ ቀላል ነው። ሌሊት የሚበራ ትንሽ መብራት ያድርጉ።
  • ብቸኝነት፦ እርስዎ ሥራ ሲሄዱ እነሱ ቀኑን ሙሉ ብቻቸውን ቤት ይውላሉ። ቋንቋው አዲስ ነው፤ ጎረቤት አያውቁም። ብቸኝነት እንቅልፍን ይረብሻል፣ ስሜትንም ያወርዳል። በቤተክርስቲያን ወይም በመስጊድ ከሀበሻ ማህበረሰብ ጋር ያገናኟቸው፤ ኢትዮጵያ ላሉ ቤተሰቦቻቸውም በየቀኑ እንዲደውሉ ያመቻቹላቸው።
ኢመርጀንሲና ክፍያ
  • እውነተኛ ኢመርጀንሲ ከሆነ በክፍያ ፍርሃት አይዘግዩ። ኢንሹራንስ ባይኖርም፣ የሆስፒታል ኢመርጀንሲ ሩም መርምሮ ሁኔታቸው እስኪረጋጋ ማከም ግዴታ አለበት። ሕጉ (EMTALA) እንደዚህ ነው።
  • ለቀላል ሕመም፦ አርጀንት ኬር (urgent care) ከኢመርጀንሲ ሩም በጣም ይረክሳል።
  • ቢል ከመጣ፦ ሆስፒታሉን ፋይናንሻል አሲስታንስ (financial assistance) እንዳለው ይጠይቁ። ብዙ ሆስፒታሎች ይህ ፕሮግራም አላቸው፤ ማን እንደሚያገኘው ከሆስፒታል ሆስፒታል ይለያያል።
ሐኪም መቼ ማየት?
  • ከጉዞው በፊት፣ ደም ግፊታቸውና ስኳራቸው ኮንትሮል መሆኑን ለማረጋገጥ።
  • መድኃኒታቸው ሊያልቅ ሲቃረብ፣ ሊስቱን ይዘው እዚህ ያለ ሐኪም ጋር።
  • አንድ እግር ካበጠ ወይም ካመመ፣ በዚያው ቀን።
  • እንቅልፍ ካጡ፣ ምግብ ካልበሉ ወይም ስሜታቸው ለሳምንታት ከወረደ።
ለሐኪምዎ የሚጠይቋቸው
  • ደም ግፊቴና ስኳሬ ለረጅም ጉዞ ዝግጁ ናቸው?
  • ለጉዞው የክሎት ሪስኬ ከፍ ያለ ነው? ምን ላድርግ?
  • መድኃኒቴን በአዲሱ ሰዓት እንዴት ልውሰድ? ኢንሱሊኔንስ?
  • ለዕድሜዬ የሚሆነው የፍሉ ክትባት የቱ ነው?
ምንጮች
  • CDC. Blood Clots and Travel: What You Need to Know.
  • U.S. Customs and Border Protection. Traveling with medication.
  • U.S. Food and Drug Administration. Traveling with Prescription Medications.
  • Centers for Medicare & Medicaid Services. Emergency Medical Treatment & Labor Act (EMTALA).
  • Internal Revenue Service. Financial Assistance Policies (501(r)) for charitable hospitals.
  • American Heart Association. Cold weather and cardiovascular disease.

ጥያቄዎችና መልሶች

የመጀመሪያውን ጥያቄ ይጠይቁ።

ጥያቄዎ ከታየ በኋላ እዚህ ይወጣል። · Your question appears after it is checked.

ተያያዥ ርዕሶች

በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው፤ የግል የሕክምና ምክር አይደለም። ድንገተኛ ችግር ካለ 911 (አሜሪካ) ወይም 907 (አዲስ አበባ)።
ሁሉም ጽሑፎች · ስለ እኛ · ያግኙን