ሕክምናHikimna · Amharic health reference
በሕክምና ባለሙያ የተገመገመ። ለትምህርት ብቻ ነው። Reviewed by a medical professional. Educational only.
4

ቃር (ሃርትበርን)

Heartburn

በሕክምና ባለሙያ የተገመገመ · Reviewed by a medical professional · 2026-09-20

ምንድን ነው?

ደረትዎ ላይ የሚያቃጥል ስሜት ተሰምቶዎት ያውቃል? ብዙዎቻችን ቃር ወይም ሃርትበርን (heartburn) እንለዋለን። ይህ የሚሆነው የጨጓራ አሲድ (stomach acid) ወደ ላይ ወደ ምግብ ቧንቧ (esophagus) ሲመለስ ነው። አንዳንዴ መራራ ወይም ኮምጣጣ ፈሳሽ እስከ ጉሮሮ ድረስ ይመጣል።

አደገኛ ምልክቶች

  • ደረት ላይ የሚጫን ህመም ከላብና ከትንፋሽ ማጠር ጋር ከመጣ። ይህ ቃር ሳይሆን የልብ ችግር (heart attack) ሊሆን ይችላል፤ ወዲያውኑ 911 (US) ወይም 907 (አዲስ አበባ) ይደውሉ።
  • ደም ማስመለስ፣ ወይም ጥቁር እንደ ሬንጅ ያለ ሰገራ።
  • ምግብ መዋጥ ከከበደዎ ወይም ክብደትዎ ያለ ምክንያት ከቀነሰ ሳይዘገዩ ወደ ሕክምና ይሂዱ።

ቤት ውስጥ

  • በአንድ ጊዜ ብዙ ከመብላት ይልቅ ትንሽ ትንሽ ብለው ደጋግመው ይመገቡ።
  • ከመተኛትዎ በፊት ቢያንስ ሦስት ሰዓት ቀደም ብለው እራት ይብሉ። እንደበሉ ወዲያውኑ አይተኙ።
  • ሲተኙ የላይኛውን የሰውነትዎን ክፍል ከፍ ያድርጉ፤ አሲዱ ወደ ላይ እንዳይመለስ ይረዳል።
  • ቅመም የበዛበት ወጥ፣ ቅባት ያለው ምግብ ወይም ቡና ቃር የሚቀሰቅስብዎ ከሆነ ይቀንሱ።
  • አልኮል ይቀንሱ፤ ማጨስ ያቁሙ።
  • ከፋርማሲ የሚገዛ የአሲድ መድኃኒት ለሳምንታት ብቻዎን አይውሰዱ፤ ህመሙ መጥፋቱ ችግሩ መጥፋቱ አይደለም። ከሁለት ሳምንት በላይ የሚያስፈልግዎ ከሆነ ሐኪም ያማክሩ።
ምልክቶች
  • ከደረት አጥንት ጀርባ ወደ ላይ የሚወጣ ማቃጠል፤ በተለይ ከምግብ በኋላ ወይም ሲተኙ።
  • መራራ ወይም ኮምጣጣ ፈሳሽ እስከ ጉሮሮ መምጣት።

ቀስቃሾቹ፦

  • ቅመም የበዛበት ወጥ፣ ቅባት የበዛበት ምግብ እና ቡና ለአንዳንዶቻችን።
  • ከመጠን በላይ መብላትና እንደበላን ወዲያውኑ መተኛት፤ እነዚህ ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው።
  • አልኮል መጠጣትና ሲጋራ ማጨስ የበሩን ጡንቻ ያዝላሉ።
ሐኪም መቼ ማየት?
  • ቃሩ በሳምንት ከሁለት ጊዜ በላይ የሚደጋገም ከሆነ።
  • አመጋገብንና አኗኗርን ካስተካከሉ በኋላም የማይቀንስ ከሆነ።
  • ምግብ መዋጥ ከከበደዎ፣ ክብደትዎ ያለ ምክንያት ከቀነሰ፣ ወይም ደም ካስመለሰዎ ሳይዘገዩ።
  • የአሲድ መድኃኒት ከሁለት ሳምንት በላይ የሚያስፈልግዎ ከሆነ።
መከላከያ
  • ከመጠን በላይ አይብሉ፤ ትንሽ ትንሽ ብለው ደጋግመው ይመገቡ።
  • እራትን ከመተኛት ሦስት ሰዓት በፊት ይብሉ።
  • ቀስቃሽ ምግቦችን (ቅመም፣ ቅባት፣ ቡና) ይቀንሱ።
  • አልኮል ይቀንሱ፤ ማጨስ ያቁሙ።
  • ጤናማ ክብደት ይጠብቁ።
ለሐኪምዎ የሚጠይቋቸው
  • ቃሬ ጌርድ (GERD) ነው?
  • መድኃኒት ያስፈልገኛል? ለምን ያህል ጊዜ?
  • ኢንዶስኮፒ ("ካሜራ") ምርመራ ያስፈልገኛል?
  • የምወስዳቸው ሌሎች መድኃኒቶች ቃርን ያባብሳሉ?
ምንጮች

ጥያቄዎችና መልሶች · 4

452f…

ቲማቲም ስበላ ደረት አከባቢ ያቃጥለኛል ዶክተር ለምንድነው?

ሕክምና

ቲማቲም አሲዳማ ስለሆነ የጨጓራ አሲድ ወደ ጉሮሮ እንዲመለስ ሊያደርግ ይችላል፣ ያ ማቃጠል ብዙ ጊዜ ከዚያ ነው። ቡና፣ ቅመም የበዛበትና ቅባታማ ምግብም እንዲሁ ያደርጋሉ። ትንሽ ትንሽ መብላትና ከመተኛት በፊት ሦስት ሰዓት ያህል አለመመገብ ይረዳል። ማቃጠሉ በየቀኑ ካለ ወይም መዋጥ ከከበደ ምርመራ ያስፈልጋል።

dang…

Ene black chocolate 🍫 sbela yetewegi chegura ynesabgim banana 🍌 edezaw i love avocado 🥑

ሕክምና

Chocolate yegudguadun mezgia jimat silemiyalala asid wede laiy yimetal. Tinish arigew ena ke migib behuala bitiblut yishalal. Muz degmo yalbesele sihon hodin yinefal, yebesele muz gin yishalal.

user88…

ለጨጓራ አጠቃቀሙን ብታብራራልን አንድ የሻይ ማንኪያ ሱማክ በውሀ ብርጭቆ ወይስ በሻይ ብርጭቆነው ?ስጠጣውስ በባዶ ሆድ

ሕክምና

ባዶ ሆድ ላይ አይጠጡት፤ ኮምጣጣ ስለሆነ ጨጓራን ያበሳጫል። ጨጓራን የሚያክም መጠን የለውም፤ ሱማክ ማጣፈጫ ነው፣ በምግብ ላይ ተነስንሶ ይበላ።

user87…

ሠላም ዶክተረ አንገቴ ላይ እየመጣ ሚወተፍ ነገር እየተሠማኝ ሀኪም ቤት ሂጀ ጨጓራ ነው ተባልኩ ግን እየቆየ ሲመጣ እያነቀኝ ሄደ ምን ሊሆን ይችላል እባክህ

ሕክምና

የሆድ አሲድ ወደ ላይ ሲመጣ ጉሮሮ ላይ የመወተፍ ስሜት ይሰጣል፣ ከበሉ በኋላ ወዲያው አለመተኛት ይረዳል። ግን እየባሰ ከሄደ፣ ምግብ መዋጥ ከከበደ ወይም ክብደት ከቀነሰ ጉሮሮው በካሜራ መታየት አለበት።

ጥያቄዎ ከታየ በኋላ እዚህ ይወጣል። · Your question appears after it is checked.

ተያያዥ ርዕሶች

በሕክምና ባለሙያ የተገመገመ። ለትምህርት ብቻ ነው፤ የግል የሕክምና ምክር አይደለም። ድንገተኛ ችግር ካለ 911 (አሜሪካ) ወይም 907 (አዲስ አበባ)።
ሁሉም ጽሑፎች · ስለ እኛ · ያግኙን