ሕክምናHikimna · Amharic health reference
በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው። Written by an MD. Educational only.
10

የደም ግፊት

High Blood Pressure (Hypertension)

በሐኪም (MD) የተጻፈ · Written by an MD · 2026-09-20

ምንድን ነው?

ልብ ደምን ወደ መላው ሰውነት ሲገፋ፣ ደሙ በደም ሥሮች ግድግዳ ላይ የሚፈጥረው ኃይል የደም ግፊት (blood pressure) ይባላል። ይህ ግፊት በተደጋጋሚ ከፍ ብሎ ሲቆይ፣ ሃይፐርቴንሽን (hypertension) ይባላል።

መለኪያው ሁለት ቁጥሮች አሉት። የላይኛው ቁጥር፣ ሲስቶሊክ (systolic)፣ ልብ ደምን ሲገፋ የሚፈጠረውን ግፊት ያሳያል። የታችኛው ቁጥር፣ ዳያስቶሊክ (diastolic)፣ ልብ በምቶች መካከል ሲያርፍ ያለውን ግፊት ያሳያል። ሁለቱም ቁጥሮች አስፈላጊ ናቸው።

  • በአሜሪካ AHA/ACC መመሪያ፣ መደበኛ የደም ግፊት የላይኛው ከ120 እና የታችኛው ከ80 mmHg በታች ነው። 130/80 ወይም በላይ ከፍተኛ ግፊት ተብሎ ይመደባል፤ WHO ለምርመራ 140/90 ወይም በላይ በተለያዩ ቀናት መገኘትን ይጠቀማል። የሕክምና ውሳኔ በተደጋጋሚ መለኪያና በግል የጤና ሁኔታ ይወሰናል።
  • በዓለም ጤና ድርጅት መለኪያ፣ በሁለት የተለያዩ ቀናት የላይኛው 140 ወይም ከዚያ በላይ፣ ወይም የታችኛው 90 ወይም ከዚያ በላይ ሆኖ ከተደጋገመ፣ የደም ግፊት በሽታ ሊኖር ይችላል።
  • አንድ ጊዜ ከፍ ብሎ መለካቱ ብቻ በሽታ አለ ማለት አይደለም።

አደገኛ ምልክቶች

ከሚከተሉት አንዱ ካለ ወዲያውኑ እርዳታ ይፈልጉ፦

  • የላይኛው ቁጥር 180 ወይም ከዚያ በላይ፣ ወይም የታችኛው 120 ወይም ከዚያ በላይ፣ ከደረት ህመም፣ ከትንፋሽ ማጠር ወይም ከከባድ ራስ ምታት ጋር።
  • 180/120 ወይም ከዚያ በላይ ሆኖ ምንም ምልክት ከሌለ፣ አንድ ደቂቃ ጠብቀው እንደገና ይለኩ፤ ሁለተኛውም መለኪያ ከፍ ካለ በተቻለ ፍጥነት ሐኪምዎን ያነጋግሩ።
  • የፊት መጣመም፣ የአንዱ እጅ መዛል፣ የንግግር መደናቀፍ። እነዚህ የስትሮክ (stroke) ምልክቶች ናቸው።
  • ድንገተኛ የዓይን ዕይታ መጥፋት።

ቤት ውስጥ ምን ማድረግ?

  • ትክክለኛ መለኪያ ለማግኘት አቀማመጥ ወሳኝ ነው። ከመለካትዎ ሠላሳ ደቂቃ በፊት ቡና አይጠጡ፣ አያጨሱ፣ እንቅስቃሴም አያድርጉ።
  • ተቀምጠው፣ ጀርባዎን ደግፈው፣ እግርዎን መሬት ላይ አድርገው፣ እጅዎን በልብ ደረጃ ያስቀምጡ። አምስት ደቂቃ ያርፉ።
  • በሁለት የተለያዩ ቀናት ይለኩ። ውጤቱን ጽፈው ለሐኪምዎ ይውሰዱ።
  • ጨው ይቀንሱ፣ በየቀኑ ይንቀሳቀሱ፣ ጫትና አልኮል ያስወግዱ።
  • የታዘዘልዎትን መድኃኒት ምልክት ባይሰማዎትም አያቋርጡ።
ምልክቶች

ብዙ ሰዎች ራስ ምታት እስኪጀምራቸው ይጠብቃሉ። እውነታው ግን፣ የደም ግፊት በሽታ ለዓመታት ያለ ምልክት ልብን፣ አንጎልን፣ ኩላሊትንና ዓይንን ሊጎዳ ይችላል። ለዚህም ነው ጸጥተኛ አደጋ የሚባለው። ብቸኛው መንገድ መለካት ነው።

ሐኪም መቼ ማየት?
  • መለኪያዎ በተደጋጋሚ 130/80 ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ፣ ስለ ቀጣይ ክትትል ሐኪምዎን ያማክሩ። ቁጥሩ ብቻውን መድኃኒት መጀመር ማለት አይደለም።
  • እርጉዝ ከሆኑና የደም ግፊትዎ ከፍ ካለ። ይህ ፕሪኤክላምፕሲያ (preeclampsia) ሊሆን ይችላል።
  • መድኃኒት እየወሰዱ ግፊቱ ካልቀነሰ፣ ወይም መድኃኒቱ ማዞር ወይም ድካም ካመጣ።

የግል ግብዎ በዕድሜዎና በሌሎች የጤና ሁኔታዎች ሊለያይ ስለሚችል፣ ከሐኪምዎ ጋር ይወስኑ።

መከላከያ
  • ጨው በቀን ከአንድ የሻይ ማንኪያ በታች።
  • በሳምንት ቢያንስ 150 ደቂቃ መራመድ ወይም መንቀሳቀስ።
  • ክብደት መቀነስ፣ ማጨስ ማቆም፣ አልኮል መቀነስ።
  • ከ40 ዓመት በኋላ በዓመት አንድ ጊዜ መለካት፤ የቤተሰብ ታሪክ ካለ ቀደም ብሎ።
ለሐኪምዎ የሚጠይቋቸው
  • የእኔ የደም ግፊት ግብ ስንት ነው?
  • ቤት ውስጥ መለካት አለብኝ? በምን ያህል ጊዜ?
  • ይህ መድኃኒት ከሌሎች መድኃኒቶቼ ጋር ችግር አለው?
  • ኩላሊቴንና ዓይኔን መመርመር አለብኝ?
ምንጮች

ጥያቄዎችና መልሶች · 10

wola

የደም ግፊቴ ከኖርማል በታች 90/60 በዛ ሬንጅ አካባቢ ነው የጤና ችግር ይኖረዋል

ሕክምና

90/60 አካባቢ መሆኑ ብቻ ሁልጊዜ በሽታ ማለት አይደለም። ማዞር፣ መሳት ወይም ድካም አለ? እነዚህ ከተደጋገሙ ምክንያቱን ማስመርመር ያስፈልጋል። ደም ማነስ መሆኑም በግፊት ቁጥር ብቻ አይታወቅም።

saba

Thank you doctor. I take 5mg lisinopril. Can I eat banana and salad

ሕክምና

Yes, normal portions of banana and salad are fine with lisinopril. The drug makes your body hold on to a bit more potassium, so the things to skip are potassium supplements and salt substitutes like Lo Salt. Food only becomes a problem if your kidneys are weak.

user11

በጣም ይነስርኛል እና ምን ትለኛለህ በናትህ እዳታልፈኝ

ሕክምና

በሙቀት ወይም በደረቅ አየር ወቅት የአፍንጫ ውስጥ የደም ስሮች ቶሎ ሊፈነዱ ይችላሉ። ሲነክር ጭንቅላትን ወደ ፊት አድርገው የአፍንጫውን ለስላሳ ክፍል ለ10 ደቂቃ ያህል ቆንጥጠው ይያዙ፤ ወደ ኋላ አያዘንብሉ። መድማቱ ከ20 ደቂቃ በላይ ከቆየ፣ ራስ ካዞረ ወይም በተደጋጋሚ የሚከሰት ከሆነ ግን የደም ግፊትንና አፍንጫን ለመመርመር ወደ ጤና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል።

soul

ቀይ ስጋ ማለት ነጭ ስጋስ እንብላ? ምን ማለት ነው?

ሕክምና

ቀይ ስጋ የበሬ፣ የበግና የፍየል ስጋ ነው፤ ዶሮና አሳ ደግሞ ነጭ ስጋ ይባላሉ። ደም ግፊት ካለ ከቀይ ስጋ ይልቅ አሳና ቆዳው የተገፈፈ ዶሮ ይሻላል፤ ቀይ ስጋ ሲበላም ስቡ የወጣለትን በትንሹ፣ በሳምንት ጥቂት ጊዜ ብቻ።

abiy

እንቁላልስ

ሕክምና

እንቁላል ደም ግፊትን አያስነሳም፤ ለአብዛኛው ሰው በቀን አንድ እንቁላል ችግር የለውም። ጥንቃቄው ከእንቁላሉ ጋር በሚበላው ጨው፣ ቅቤና ዘይት ላይ ነው፤ ቀቅሎ መብላት ይሻላል።

user81

የደም ግፊትንስ የከላከላል ወይ

ሕክምና

ሞሪንጋ ደም ግፊትን በትንሹ እንደሚቀንስ የሚያሳዩ ትናንሽ ጥናቶች አሉ፤ ማስረጃው ግን ገና ጠንካራ አይደለም። ጨው መቀነስ፣ ክብደት መቀነስና በየቀኑ መራመድ ከሞሪንጋ በላይ እርግጠኛ ውጤት አላቸው።

ab65

ለደምግፊት ግንዱንም ቅጠሉንም በአድላይ በጁስመልክ ይፈጭ?ለያይተን ነው?ንገረን

ሕክምና

አብረው ቢፈጩ ችግር የለውም፤ ቅጠሉ የበለጠ ማዕድን ስላለው አብሮ መግባቱ ይሻላል። ግን ሴለሪ የደም ግፊት መድኃኒትን አይተካም፤ ግፊትን በእርግጥ የሚያወርደው ጨውን መቀነስ ነው።

user26

ከርካዴ የደም ኪኒን የሚወስድ መጠቀም ይችላል? የስኳር መድኃኒት የሚወስድስ?

ሕክምና

ከርካዴ ግፊትንም ስኳርንም ትንሽ ሊያወርድ ስለሚችል ከመድኃኒቱ ጋር ተደምሮ ከመጠን በላይ ሊያወርድ ይችላል። በቀን በአንድ ሲኒ ይጀምሩና ግፊትና ስኳርዎን ይለኩ፤ ማዞር ወይም መንቀጥቀጥ ካለ ያቁሙት። መድኃኒቱን ግን አያቋርጡ።

kume

ወንድሜ ትክክለኛ ያለብኝን ነገር እዳለ ተናግረኸዋል እሺ በምን እንቆጣጠረው መፍትሄ ምን አለው

ሕክምና

ጨው መቀነስ፣ በየቀኑ ግማሽ ሰዓት በእግር መራመድና ክብደት መቀነስ ግፊትን በደንብ ያወርዳሉ። መድኃኒት ከታዘዘልዎ ደግሞ ጤና ቢሰማዎትም በየቀኑ ሳያቋርጡ ይውሰዱ።

bloo

በጣም ስናደድ ወይም ስጨነቅ ማጅራቴን ያቃጥለኛል ምንድነው

ሕክምና

በንዴትና በጭንቀት ጊዜ የአንገትና የማጅራት ጡንቻ ስለሚወጠር ነው ማቃጠሉ የሚመጣው። ግፊት እንዳለብዎ ለማወቅ ግን ተረጋግተው ባረፉበት ሰዓት ይለኩት።

ጥያቄዎ ከታየ በኋላ እዚህ ይወጣል። · Your question appears after it is checked.

ተያያዥ ርዕሶች

በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው፤ የግል የሕክምና ምክር አይደለም። ድንገተኛ ችግር ካለ 911 (አሜሪካ) ወይም 907 (አዲስ አበባ)።
ሁሉም ጽሑፎች · ስለ እኛ · ያግኙን