ሃሺሞቶ ታይሮዳይተስ
Hashimoto Thyroiditis
በሐኪም (MD) የተጻፈ · Written by an MD · 2026-09-20
ምንድን ነው?
ሃሺሞቶ ታይሮዳይተስ (Hashimoto thyroiditis) የመከላከያ ሥርዓታችን በራሱ ታይሮይድ (thyroid) ላይ ጥቃት የሚያደርስበት የአውቶኢሚውን (autoimmune) በሽታ ነው። ታይሮይድ በአንገት ፊት የሚገኝ፣ የቢራቢሮ ቅርጽ ያለው ትንሽ እጢ ነው። የሰውነትን ኃይል፣ ሙቀትና የልብ ሥራ የሚቆጣጠሩ ሆርሞኖችን ያመነጫል።
አንቲቦዲዎች (antibodies) ታይሮይዱን ቀስ በቀስ ይጎዳሉ። በዚህ ምክንያት እጢው በቂ ሆርሞን ማምረት ያቆማል፤ ይህ ሃይፖታይሮዲዝም (hypothyroidism) ይባላል። ሂደቱ ቀስ ያለ ስለሆነ በመጀመሪያ ምልክት ላይኖር ይችላል።
ሃሺሞቶ ብዙ ጊዜ በሴቶች ላይ ይታያል፣ በቤተሰብ ውስጥም ሊደጋገም ይችላል። በዲያስፖራ ውስጥ ድካምና ክብደት መጨመር ብዙ ጊዜ በሥራ ጫና ወይም በብርድ ወቅት ይታማል። ቀላል የደም ምርመራ ግን የታይሮይድ ችግር መሆኑን ሊያሳይ ይችላል።
አደገኛ ምልክቶች
ሃሺሞቶ ብዙ ጊዜ ቀስ በቀስ የሚመጣ በሽታ ነው። ሆኖም ከሚከተሉት አንዱ ካለ ወዲያውኑ እርዳታ ይፈልጉ፦
- የአንገት እብጠቱ የመተንፈስ ወይም የመዋጥ ችግር ሲያመጣ።
- ከባድ ድካም ከግራ መጋባት፣ ከከባድ ብርድ ወይም ከእንቅልፍ ማብዛት ጋር፤ በተለይ መድኃኒት ካቋረጡ በኋላ።
- የልብ ምት በጣም ሲቀንስ ወይም ራስን ሲስቱ።
ቤት ውስጥ ምን ማድረግ?
- ሌቮታይሮክሲን (levothyroxine) ከታዘዘ በየቀኑ በተመሳሳይ ሰዓት ይውሰዱ። በራስዎ አያቋርጡ፣ መጠኑንም አይቀይሩ።
- መድኃኒቱ በሐኪምና በደም ምርመራ መስተካከል አለበት። የክትትል የደም ምርመራዎን አያሳልፉ።
- ሆርሞኑ መደበኛ ከሆነ ክትትል ብቻ ሊበቃ ይችላል። ይህ ማለት ግን ችላ ማለት አይደለም፤ በየጊዜው ይመርመሩ።
- አዮዲን (iodine) ወይም የታይሮይድ ማሟያ (supplement) በራስዎ አይውሰዱ።
- ምልክቶችዎን ጽፈው ለሐኪምዎ ይውሰዱ።
ምልክቶች
- ድካም።
- ክብደት መጨመር።
- ብርድ አለመቻል።
- ድርቀት (constipation)።
- የቆዳ መድረቅ።
- የፀጉር መሳሳት።
- የማተኮር ችግር።
- የወር አበባ መዛባት።
- አንገት ላይ እብጠት ወይም ጎይተር (goiter)፣ ወይም የመዋጥ ችግር።
ሐኪም መቼ ማየት?
- ድካም፣ ክብደት መጨመር፣ ብርድ አለመቻል ወይም ሌሎች ምልክቶች ካሉዎት።
- አንገትዎ ካበጠ ወይም የመዋጥ ችግር ካለ።
- እርጉዝ ከሆኑ ወይም ለማርገዝ ካሰቡ፤ የታይሮይድ ሆርሞን ለእርግዝና አስፈላጊ ነው።
- ምርመራው ቲኤስኤች (TSH)፣ ፍሪ ቲ4 (free T4) እና ቲፒኦ አንቲቦዲ (TPO antibody) የደም ምርመራዎችን ያካትታል፤ አንዳንድ ጊዜ አልትራሳውንድ (ultrasound) ይደረጋል።
መከላከያ
- ሃሺሞቶ የአውቶኢሚውን በሽታ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ መከላከል አይቻልም። ውስብስብ ችግሮቹን ግን መከላከል ይቻላል።
- በቤተሰብ ውስጥ የታይሮይድ ችግር ካለ ቀድመው ይመርመሩ።
- ምልክቶችን ችላ አይበሉ፤ ቀድሞ መታከም የልብንና የሰውነትን ጤና ይጠብቃል።
- መድኃኒትዎን በመደበኛነት ይውሰዱ፤ ክትትልዎን ይቀጥሉ።
ለሐኪምዎ የሚጠይቋቸው
- የደም ምርመራዬ ምን ያሳያል? መድኃኒት ያስፈልገኛል?
- የደም ምርመራውን በምን ያህል ጊዜ ልደግም?
- መድኃኒቱን ከምግብ ወይም ከሌሎች መድኃኒቶቼ ጋር እንዴት ልውሰድ?
- ልጆቼ ወይም እህቶቼ መመርመር አለባቸው?
ምንጮች
- MedlinePlus. Hashimoto Disease.
- NHS. Underactive thyroid (hypothyroidism).
ጥያቄዎችና መልሶች · 1
በታይሮይድ የሚመጣ ውፍረት ምልክት አለው?
አዎ፣ ታይሮይድ ሲዝል ከክብደት መጨመር ጋር ድካም፣ ብርድ መብዛት፣ ደረቅ ቆዳ፣ የፀጉር መሳሳትና የሆድ ድርቀት አብረው ይታያሉ። እነዚህ ካሉብዎት የታይሮይድ ምርመራ ነው የሚያረጋግጠው።
ተያያዥ ርዕሶች
በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው፤ የግል የሕክምና ምክር አይደለም። ድንገተኛ ችግር ካለ 911 (አሜሪካ) ወይም 907 (አዲስ አበባ)።
ሁሉም ጽሑፎች · ስለ እኛ · ያግኙን
እንቅርት
ድብርት፣ ምልክቶች፣ መገለልና እርዳታ ማግኘት
የወር አበባ
የተለመዱ የሕክምና ምርመራዎችን መረዳትና ለክሊኒክ ጉብኝት መዘጋጀት