ሕክምናHikimna · Amharic health reference
በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው። Written by an MD. Educational only.
4

የወር አበባ መዛባት፦ ለምን ይዘገያል፣ ይቀራል ወይም ሁለት ጊዜ ይመጣል?

Irregular periods: why a period comes early, late or not at all

በሐኪም (MD) የተጻፈ · Written by an MD · 2026-10-06

ምንድን ነው?

የወር አበባ ሳይክል (menstrual cycle) የሚቆጠረው ደም ከጀመረበት የመጀመሪያ ቀን እስከሚቀጥለው የመጀመሪያ ቀን ድረስ ነው። ለአዋቂ ሴት ከ24 እስከ 38 ቀን ያለው ሳይክል ኖርማል ነው፤ ደሙ እስከ 8 ቀን ሊቆይ ይችላል። ከወር ወደ ወር ጥቂት ቀናት መቀያየሩም ችግር አይደለም።

የወር አበባ የሚመጣው ኦቫሪ (ovary) እንቁላል ከለቀቀች ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ ነው። ይህን የሚያዘው ብሬን (brain) ውስጥ ያለ ትንሽ ማዕከል ነው። ስለዚህ ብሬንን፣ ሆርሞንን ወይም ኦቫሪን የሚነካ ማንኛውም ነገር እንቁላሉን ያዘገየዋል ወይም ጭራሹን ሊያስቀረው ይችላል። ያኔ የወር አበባው ይዘገያል፣ ይቀራል፣ ወይም ሳይጠበቅ ይመጣል።

የወር አበባ በጀመረባቸው የመጀመሪያ ዓመታትና ከአርባ ዓመት በኋላ (perimenopause) መዛባቱ የተለመደ ነው።

አደገኛ ምልክቶች

ከሚከተሉት አንዱ ካለ ወዲያውኑ 911 ይደውሉ፦

  • ፓድ በየሰዓቱ እየሞላ ከሁለት ሰዓት በላይ ከቀጠለ።
  • ራስዎን ካዞረዎት ወይም ራስዎን ከሳቱ።
  • እርጉዝ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ጠርጥረው ከባድ የሆድ ሕመምና ደም ካለ።

ቤት ውስጥ ምን ማድረግ?

  • የወር አበባዎ የጀመረበትን ቀን በስልክዎ አፕ (app) ወይም በካሌንደር ይመዝግቡ። የሦስት ወር ሪከርድ ሐኪሙን በጣም ይረዳዋል።
  • የወር አበባ ከቀረ መጀመሪያ ፕሪግናንሲ ቴስት ያድርጉ።
  • እንቅልፍ፣ ምግብና እንቅስቃሴን መደበኛ ያድርጉ፤ ከባድ ስትረስ ካለ እርዳታ ይፈልጉ።
ምልክቶች
  • ሳይክሉ ከ24 ቀን ማጠር፣ ማለትም በወር ሁለት ጊዜ መምጣት።
  • ሳይክሉ ከ38 ቀን መርዘም፣ ወይም ለወራት መቅረት።
  • ከወር ወደ ወር ቀኑ በጣም መቀያየር።
  • በወር አበባዎቹ መሃል የሚታይ ነጠብጣብ ደም (spotting)።
  • ጥቁር ወይም ቡናማ ደም፦ ብዙ ጊዜ የቆየ ደም ነው እንጂ «የቆሸሸ ደም» አይደለም።
ዋና ዋና ምክንያቶች
  • አንደኛ፣ እርግዝና። የወር አበባ ከቀረ መጀመሪያ ፕሪግናንሲ ቴስት (pregnancy test) ያድርጉ፤ ፋርማሲ ማግኘት ይቻላል፣ ቤት ውስጥ መስራት ይቻላል። ጡት እያጠቡ ከሆነም የወር አበባ መዘግየቱ ኖርማል ነው።
  • ሁለተኛ፣ ስትረስ (stress) እና ሰውነት ላይ የሚመጣ ለውጥ። ከባድ ጭንቀት፣ ሀገር መቀየር፣ የሌሊት ሥራ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ክብደት በፍጥነት መጨመር ወይም መቀነስ፣ እና በጣም ከባድ ኤክሰርሳይዝ (exercise)። ይህ ሲሆን ብሬን እንቁላሉን ለጊዜው ያቆመዋል።
  • ሦስተኛ፣ ፒ ሲ ኦ ኤስ (PCOS)። በጣም የተለመደ የሆርሞን ችግር ነው። ምልክቶቹ የሚዘገይ ወይም የሚቀር የወር አበባ፣ አገጭና ፊት ላይ የሚወጣ ፀጉር፣ ብጉርና ክብደት መጨመር ናቸው። ከኢንሱሊን (insulin) ጋር ስለሚያያዝ የስኳር ሪስክንም ከፍ ያደርጋል። ማስተካከል ወይም ማከም ይቻላል፤ ክብደትዎ ከፍ ያለ ከሆነ ጥቂት ኪሎ መቀነስ ብቻ እንኳን ሳይክሉን ሊያስተካክል ይችላል።
  • አራተኛ፣ ታይሮይድ (thyroid) እና ፕሮላክቲን (prolactin)። ታይሮይድ ከበዛም ካነሰም ሳይክሉን ያዛባል። ሳያጠቡ ከጡት ወተት የሚመስል ፈሳሽ ከወጣ ፕሮላክቲን የሚባለው ሆርሞን ከፍ ብሎ ሊሆን ይችላል። ሁለቱም በደም ቴስት ይታወቃሉ፤ ይታከማሉም።
  • አምስተኛ፣ የወሊድ መከላከያ። በተለይ ዲፖ ሾት (Depo-Provera) በመጀመሪያዎቹ ወራት ያልተጠበቀ ነጠብጣብ ደም ያመጣል፤ ከዚያ ብዙ ሴቶች ላይ የወር አበባ ጭራሹን ይቆማል። ይህ አደገኛ አይደለም። ሾቱን ካቆሙ በኋላ ግን ሳይክሉና እርግዝና እስኪመለሱ በአማካይ አስር ወር ገደማ ሊወስድ ይችላል፤ ማርገዝ ካሰቡ ቀድመው ዲፖን ያቁሙ።
«ደሙ ማሕፀን ውስጥ ይጠራቀማል?»

አይጠራቀምም። የወር አበባ ሲቀር ደም የትም አይጠራቀምም። ነገር ግን በተለይ በፒ ሲ ኦ ኤስ ለብዙ ወራት እንቁላል ካልወጣ፣ የማሕፀን ውስጠኛው ሽፋን (endometrium) ሳይፈርስ እየወፈረ ሊሄድ ይችላል። ለዚህ ነው ረጅም ጊዜ የሚቀር የወር አበባ በሐኪም መመርመር ያለበት።

ልጅ መውለድ ይቻላል?

ሳይክል መዛባት መካን ነሽ ማለት አይደለም። እንቁላል አልፎ አልፎ ስለሚወጣ ማርገዝ ይቻላል፤ ግን መቼ እንደሚወጣ ማወቅ ይከብዳል። ከ35 ዓመት በታች ከሆኑ ለአንድ ዓመት ሞክረው ካልተሳካ፣ ከ35 በላይ ደግሞ ከስድስት ወር በኋላ ሐኪም ያግኙ። ሳይክሉ በጣም የተዛባ ከሆነ ግን አይጠብቁ፤ ቀድመው ይሂዱ።

ሐኪም መቼ ማየት?
  • ቀድሞ መደበኛ የነበረው የወር አበባዎ ለሦስት ወር ከቀረ።
  • ሳይክሉ ከ24 ቀን ካጠረ ወይም ከ38 ቀን ከረዘመ።
  • በወር አበባዎቹ መሃል ወይም ከግንኙነት በኋላ ደም ከታየ።
  • ማረጥ (menopause) ከደረሱ በኋላ ምንም ዓይነት ደም ከታየ።
  • ሳያጠቡ ከጡት ፈሳሽ ከወጣ፣ ወይም ፊት ላይ ፀጉርና ብጉር ከጨመረ።

ብዙ ጊዜ የሚደረጉት ፕሪግናንሲ ቴስት፣ የታይሮይድና የሆርሞን የደም ቴስት፣ እና አልትራሳውንድ (ultrasound) ናቸው።

መከላከያ
  • ሳይክልዎን ይከታተሉ፤ ለውጥ ሲኖር ቶሎ ያስተውሉ።
  • ክብደት ከፍ ካለ ቀስ ብሎ መቀነስ ለፒ ሲ ኦ ኤስ ይረዳል።
  • ማርገዝ ካሰቡ የወሊድ መከላከያውን መቼ ማቆም እንዳለብዎ ሐኪምዎን አስቀድመው ይጠይቁ።
ለሐኪምዎ የሚጠይቋቸው
  • የወር አበባዬ የሚዛባበት ምክንያት ምንድነው?
  • ፒ ሲ ኦ ኤስ፣ ታይሮይድ ወይም ፕሮላክቲን ቴስት ያስፈልገኛል?
  • ማርገዝ ብፈልግ ምን ማድረግ አለብኝ?
  • ለእኔ የሚሆነው የወሊድ መከላከያ የቱ ነው?
ምንጮች
  • American College of Obstetricians and Gynecologists (ACOG). Abnormal Uterine Bleeding (FAQ).
  • NHS. Irregular periods.
  • NICHD (NIH). Polycystic Ovary Syndrome (PCOS).
  • ACOG. Polycystic Ovary Syndrome (PCOS) (FAQ).
  • CDC. U.S. Selected Practice Recommendations for Contraceptive Use (injectable contraception).

ጥያቄዎችና መልሶች · 4

2234

“My doctor only offered me birth control, but I don’t want to take it. Are there any other options?”

ሕክምና

There are. Diet and exercise are first line for PCOS, and even 5 to 10 percent weight loss often restores ovulation and regular periods. Non hormonal prescription options exist too, so ask what else is available.

user

የወር አበባ ከዓመት ያላነሰ ቆይቶ ነው የሚመጣው፤ ፀጉሬ ይነቃቀላል፣ ፊት ላይ ብጉር በተደጋጋሚ፣ ጺም እና ክብደቴ በጣም ይጨምራል።

ሕክምና

እነዚህ ምልክቶች አብረው ሲመጡ ብዙ ጊዜ ፒሲኦስ ነው። ዓመት ሙሉ የወር አበባ አለመምጣት ግን በራሱ መታየት አለበት፣ የሆርሞንና የስኳር ምርመራ ያስፈልጋል። እስከዚያው እንቅስቃሴና የስኳር ምግብ መቀነስ ዑደቱን ሊመልስ ይችላል።

elfe

My period is coming every 2 months. What can I do?

ሕክምና

A gap of about two months often comes from stress, big weight changes or PCOS. Take a pregnancy test first. If it keeps happening, a hormone, thyroid and ultrasound check will find the cause.

ከቲክቶክ የመጣ ጥያቄ

የወር አበባ መዛባትን እነንዴት ታየዋለሕ

ሕክምና

በየሰዓቱ ሞዴስ የሚያረጥብ ደም፣ የራስ መዞር፣ ወይም እርግዝና ሊኖር ሲችል ሕመምና ደም መፍሰስ ካለ ዛሬውኑ ወደ ሕክምና ቦታ ይሂዱ። አልፎ አልፎ መዛባት በጭንቀት፣ በክብደት ለውጥና በጡት ማጥባት የተለመደ ነው፤ ግንኙነት ካለ መጀመሪያ የእርግዝና ምርመራ እንመክራለን። ከሦስት ወር በላይ ከጠፋ፣ ከሰባት ቀን በላይ ከፈሰሰ ወይም በወር አበባ መሀል ደም ከታየ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የማህፀን ምርመራ ያድርጉ።

ጥያቄዎ ከታየ በኋላ እዚህ ይወጣል። · Your question appears after it is checked.

ተያያዥ ርዕሶች

በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው፤ የግል የሕክምና ምክር አይደለም። ድንገተኛ ችግር ካለ 911 (አሜሪካ) ወይም 907 (አዲስ አበባ)።
ሁሉም ጽሑፎች · ስለ እኛ · ያግኙን