ሕክምናHikimna · Amharic health reference
በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው። Written by an MD. Educational only.

ኤችአይቪ

HIV

በሐኪም (MD) የተጻፈ · Written by an MD · 2026-09-20

ምንድን ነው?

ኤችአይቪ (HIV) የሰውነትን ተፈጥሯዊ የበሽታ መከላከያ ስርዓት (immune system) የሚያጠቃና ነጭ የደም ሴሎችን የሚያዳክም ቫይረስ ነው። መከላከያው እየተዳከመ ሲሄድ በሽታው ኤድስ (AIDS) ወደሚባለው ደረጃ ይሸጋገራል። ይህ እንዳይሆን በጊዜ ፈጣን ሕክምና ማግኘት ያስፈልጋል።

ቫይረሱ የሚተላለፈው ጥንቃቄ በሌለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ በደም፣ በስለታም ዕቃና ከእናት ወደ ልጅ ነው። በመተቃቀፍ፣ በመጨባበጥ፣ አብሮ በመመገብ፣ መጸዳጃ በማጋራት ወይም በአየር በፍጹም አይተላለፍም።

ዛሬ ኤችአይቪ የሚታከም በሽታ ነው። መድኃኒታቸውን በትክክል የሚወስዱ ሰዎች እንደማንኛውም ሰው ረጅምና የተሟላ ሕይወት ይኖራሉ። በኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ውስጥ ትልቁ እንቅፋት ቫይረሱ ራሱ ሳይሆን ፍርሃትና መገለል (stigma) ነው። ማግለል ሰዎች እንዳይመረመሩ ስለሚያደርግ በሽታውን የመከላከል ትግላችንን ያዳክማል።

አደገኛ ምልክቶች

ከሚከተሉት አንዱ ካለ ወዲያውኑ እርዳታ ይፈልጉ፦

  • ለቫይረሱ ተጋልጠዋል ብለው ካሰቡ (ያለ ኮንዶም ግንኙነት፣ ኮንዶም መቀደድ፣ የሌላ ሰው መርፌ)። ድህረ-አደጋ መከላከያ (PEP) በ72 ሰዓታት ውስጥ መጀመር አለበት፤ በቶሎ በጀመሩ ቁጥር የተሻለ ይሠራል።
  • ኤችአይቪ ካለብዎትና ከፍተኛ ትኩሳት፣ የትንፋሽ ማጠር፣ ከባድ ራስ ምታት፣ ግራ መጋባት ወይም የማያቋርጥ ተቅማጥ ከመጣ።
  • እርጉዝ ከሆኑና ኤችአይቪ ካለብዎት፣ ወይም ምርመራ ካላደረጉ። ወዲያውኑ የእርግዝና ክትትል ይጀምሩ።

ቤት ውስጥ ምን ማድረግ?

  • የፀረ-ኤችአይቪ መድኃኒት (ART) በየቀኑ በተመሳሳይ ሰዓት በትክክል ይውሰዱ። መድኃኒቱ ሲቋረጥ ቫይረሱ ተመልሶ ይበዛል።
  • ጥሩ ስሜት ስለተሰማዎት ወይም የቫይረስ መጠንዎ ስለማይታይ መድኃኒቱን አያቁሙ።
  • መድኃኒቱን በባህል መድኃኒት ወይም በሌላ ነገር አይተኩ።
  • በየግንኙነቱ ኮንዶም ይጠቀሙ። ይህ ከሌሎች የአባላዘር በሽታዎችና ካልተፈለገ እርግዝናም ይጠብቃል።
  • መርፌ፣ ምላጭ ወይም ሌሎች ስለታም ዕቃዎችን አያጋሩ።
  • የቤተሰብ አባል ኤችአይቪ ካለበት አብሮ መብላት፣ መተቃቀፍና መጸዳጃ መጋራት ምንም ችግር የለውም። አያግልሉ።
ምልክቶች
  • ኤችአይቪ ለብዙ ዓመታት ምንም ምልክት ላያሳይ ይችላል። ሰውየው ጤነኛ ሆኖ ይታያል፤ ቫይረሱን ግን ሊያስተላልፍ ይችላል።
  • ቫይረሱ መኖሩን ለማወቅ የኤችአይቪ ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ምርመራው በደም ወይም ከአፍ በሚወሰድ ፈሳሽ ሊደረግ ይችላል።
  • ከተያዙ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ እንደ ጉንፋን ያለ ትኩሳት፣ የጉሮሮ ህመም፣ ሽፍታና ድካም ሊኖር ይችላል፤ ይህ ግን በብዙ ሰዎች ሳይስተዋል ያልፋል።
  • ያለ ሕክምና ብዙ ከቆየ በኋላ የክብደት መቀነስ፣ ተደጋጋሚ ትኩሳት፣ የሚቆይ ተቅማጥና ተደጋጋሚ ኢንፌክሽኖች ሊታዩ ይችላሉ።
ሐኪም መቼ ማየት?
  • ተጋልጠው ከሆነ ወዲያውኑ፤ PEP በ72 ሰዓታት ውስጥ መጀመር አለበት።
  • ምርመራ አድርገው የማያውቁ ከሆነ፣ ወይም አዲስ አጋር ካለዎት። የጤና ተቋማት ምርመራና ሕክምና ሚስጥራዊነትዎን ማክበር ስላለባቸው ያለ ፍርሃት ይሂዱ።
  • ውጤቱ ቫይረሱ መኖሩን ካሳየ፣ ያለምንም መዘግየት ART ይጀምሩ።
  • እርጉዝ ከሆኑ በእርግዝና ክትትል ወቅት ይመርመሩ። ተገቢ ሕክምና ቫይረሱ ወደ ልጅ የመተላለፍ አደጋን በጣም ይቀንሳል።
  • መድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት ካመጣ ወይም መውሰድ ካቆሙ አይደብቁ፤ ለሐኪምዎ ይንገሩ።
  • ተጋላጭ ከሆኑ ስለ PrEP ይጠይቁ።
መከላከያ
  • በየግንኙነቱ ኮንዶም ይጠቀሙ።
  • ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ከግንኙነት በፊት የሚወሰድ መድኃኒት (PrEP) መጠቀማቸው የተረጋገጠ የመከላከያ አማራጭ ነው።
  • ከተጋለጡ በ72 ሰዓታት ውስጥ PEP ይጀምሩ።
  • ኤችአይቪ ካለብዎት መድኃኒትዎን በታዘዘው መሠረት በትክክል ይውሰዱና የቫይረስ መጠንዎን (viral load) በምርመራ ይከታተሉ። የቫይረስ መጠኑ በምርመራ የማይገኝ ደረጃ ላይ ከደረሰና በዚያ ደረጃ ከቀጠለ፣ ኤችአይቪ በግብረ ሥጋ ግንኙነት አይተላለፍም (U=U)።
  • ስለታም ዕቃዎችን አያጋሩ።
  • ከጋብቻ ወይም ከአዲስ ግንኙነት በፊት አብረው ይመርመሩ።
  • ነፍሰጡር እናቶች ምርመራና ሕክምና በማድረግ ልጃቸውን ይጠብቃሉ።
  • ማግለልን ያቁሙ። መገለል ሰዎች እንዳይመረመሩና እንዳይታከሙ ያደርጋል።
ለሐኪምዎ የሚጠይቋቸው
  • የቫይረስ መጠኔ ስንት ነው? መቼ የማይታይ ይሆናል?
  • መድኃኒቱን አንድ ቀን ከረሳሁ ምን ላድርግ?
  • አጋሬ PrEP መውሰድ አለበት?
  • ልጅ መውለድ እፈልጋለሁ፤ ልጄን እንዴት እጠብቃለሁ?
ምንጮች

ጥያቄዎችና መልሶች

የመጀመሪያውን ጥያቄ ይጠይቁ።

ጥያቄዎ ከታየ በኋላ እዚህ ይወጣል። · Your question appears after it is checked.

ተያያዥ ርዕሶች

በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው፤ የግል የሕክምና ምክር አይደለም። ድንገተኛ ችግር ካለ 911 (አሜሪካ) ወይም 907 (አዲስ አበባ)።
ሁሉም ጽሑፎች · ስለ እኛ · ያግኙን