የተለመዱ የዓይን ችግሮች፦ ድራይ አይ፣ የዓይን ቆብ እብጠት፣ መርገብገብና ትርፍ ሥጋ
Common eye complaints: dry eye, styes, eyelid twitching and pterygium
በሐኪም (MD) የተጻፈ · Written by an MD · 2026-09-23
ምንድን ነው?
ስልክ ወይም ኮምፒውተር ሲያዩ ዓይንዎ ይቆረቁራል? የዓይንዎ ጠርዝ ያሳክካል? የዓይን ቆብዎ ላይ እብጠት ደጋግሞ ይወጣል? እነዚህ ብዙዎቻችሁ በኮመንት የጠየቃችሁን አራት የተለመዱ የዓይን ችግሮች ናቸው። አብዛኛዎቹ አደገኛ አይደሉም፣ መፍትሔያቸውም ቤት ውስጥ ይጀምራል።
አንደኛ፣ ድራይ አይ (dry eye) እና የጠርዝ ማሳከክ (blepharitis)። ዓይናችን በእያንዳንዱ ጭፍን እርጥበት ያገኛል። ስክሪን ስናይ ግን የምንጨፍነው ከተለመደው ግማሽ ያህል ብቻ ነው፤ ያኔ የዓይኑ ላይ ያለው የእንባ ሽፋን ይተናል፣ ዓይኑ እንደ አሸዋ ይቆረቁራል፣ ጠርዙም ያሳክካል።
ሁለተኛ፣ የዓይን ቆብ እብጠት (stye ወይም chalazion)። በዓይን ቆብ ጠርዝ ላይ ትናንሽ የዘይት ቀዳዳዎች አሉ። እነዚህ ሲደፈኑ ቆቡ ላይ ትንሽ እብጠት ይወጣል። አንዳንዴ ያማል፣ አንዳንዴ ግን ሕመም የሌለው ጠጣር እብጠት ሆኖ ለሳምንታት ይቆያል።
ሦስተኛ፣ የዓይን ቆብ መርገብገብ (eyelid twitching)። ቆቡ ራሱ ብቻውን ይርገበገባል። አደገኛ አይደለም፤ ብዙ ጊዜ ምክንያቱ እንቅልፍ ማጣት፣ ስትረስ (stress) እና ካፌይን (caffeine) ነው።
አራተኛ፣ ዓይን ላይ ቀስ ብሎ የሚያድግ ትርፍ ሥጋ (pterygium)። በዓይኑ ነጭ ክፍል ላይ፣ ብዙ ጊዜ ከአፍንጫ በኩል ጀምሮ ወደ ጥቁሩ ክፍል የሚያድግ ሥጋ ነው። ፀሐይና አቧራ ያመጡታል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የሚታይ ችግር ነው። ብዙ ጊዜ ጉዳት የለውም።
አደገኛ ምልክቶች
ከሚከተሉት አንዱ ካለ ዛሬውኑ ኢመርጀንሲ (emergency) ይሂዱ፤ ይህ ጊዜ አይሰጥም፦
- ድንገት እይታ (vision) መቀነስ ወይም መጥፋት።
- ዓይን ቀልቶ ከባድ ሕመም (severe pain) ሲኖር።
- እንደ መብረቅ ያለ ፍላሽ (flash) ወይም ብዙ አዲስ ተንሳፋፊ ነጥቦች ማየት።
- መጋረጃ የመሰለ ጥላ (shadow) ከእይታዎ ላይ ሲወርድ።
ቤት ውስጥ ምን ማድረግ?
- ስክሪን ሲያዩ፣ በየሃያ ደቂቃው ለሃያ ሰከንድ ሩቅ ነገር ይመልከቱ፤ ሆን ብለው ይጨፍኑ።
- ለድራይ አይና ለጠርዝ ማሳከክ፣ ጠዋትና ማታ ሞቅ ያለ ንጹህ ጨርቅ በተጨፈነ ዓይንዎ ላይ ለአምስት ደቂቃ ያድርጉ፣ ከዚያ የቆቡን ጠርዝ በንጹህ ውሃ ቀስ ብለው ያጽዱ። አርቲፊሻል ቲርስ (artificial tears) የሚባል ጠብታ ያለ ፕሪስክሪፕሽን ከፋርማሲ ይገኛል፤ በቀን ጥቂት ጊዜ መጠቀም ይችላሉ።
- ለዓይን ቆብ እብጠት፣ በቀን ሁለቴ ሞቅ ያለ ጨርቅ አድርገው ቀስ ብለው ይሹት። አይጨምቁት፣ በመርፌ አይንኩት። አብዛኛው በሳምንታት ውስጥ ራሱ ይጠፋል።
- ለመርገብገብ፣ እንቅልፍዎን ያሟሉ፣ ቡናውን ይቀንሱ፣ ስትረስዎን ያቅልሉ።
- ለትርፍ ሥጋ፣ ውጭ ሲወጡ ሳንግላስ (sunglasses) ያድርጉ፣ ከአቧራና ከነፋስ ይጠበቁ። ደረቅ ሲል አርቲፊሻል ቲርስ ይረዳል።
ምልክቶች
- እንደ አሸዋ የመቆርቆር ስሜት፣ መቅላትና ማሳከክ፣ በተለይ ስክሪን ካዩ በኋላ ወይም ማታ ላይ።
- የዓይን ቆብ ጠርዝ ማሳከክና ጠዋት ላይ የተጣበቀ ቅርፊት።
- የዓይን ቆብ ላይ ትንሽ ቀይ የሚያም እብጠት፣ ወይም ሕመም የሌለው ጠጣር እብጠት።
- የዓይን ቆብ ብቻውን መርገብገብ፣ ብዙ ጊዜ ለሰከንዶች ወይም ለደቂቃዎች።
- በዓይኑ ነጭ ክፍል ላይ ቀስ ብሎ የሚያድግ ቢጫማ ወይም ሥጋማ ነገር።
ሐኪም መቼ ማየት?
- ከላይ ካሉት አደገኛ ምልክቶች አንዱ ካለ ዛሬውኑ።
- የዓይን ቆብ እብጠቱ በሳምንታት ካልቀነሰ፣ እያደገ ከሆነ፣ ወይም ቆቡ ሙሉ በሙሉ ቀልቶ ካበጠ።
- ትርፍ ሥጋው እያደገ ከሆነ ወይም ወደ ጥቁሩ ክፍል ተጠግቶ እይታን መሸፈን ከጀመረ፤ የዓይን ሐኪም በቀላል ቀዶ ሕክምና ያስወግደዋል።
- መርገብገቡ ከሳምንታት በላይ ካልቆመ፣ ሙሉ ዓይንዎ ከተጨፈነ፣ ወይም የፊትዎ ሌላ ክፍል አብሮ ከተንቀሳቀሰ።
- ድራይ አይ በቤት እንክብካቤ ካልተሻለ፣ ወይም ኮንታክት ሌንስ የሚጠቀሙ ከሆነ።
መከላከያ
- ስክሪን ላይ ረጅም ሰዓት አይቆዩ፤ የሃያ ደቂቃው እረፍት ዓይንዎን ይጠብቃል።
- ማታ ስልክ በጨለማ ውስጥ ከመመልከት ይቆጠቡ፤ የክፍሉን መብራት ያብሩ።
- ፀሐይ ውስጥና አቧራማ ቦታ ሳንግላስ ያድርጉ።
- ዓይንዎን በቆሸሸ እጅ አያሹ፤ የዓይን ቆብ ጠርዝ ንጹህ ይሁን።
- በቂ እንቅልፍ ይተኙ፣ ቡናና ኢነርጂ ድሪንክ ይቀንሱ።
ለሐኪምዎ የሚጠይቋቸው
- የእኔ ችግር ድራይ አይ ነው ወይስ የጠርዝ ኢንፌክሽን?
- የትኛው ጠብታ ለእኔ ይመቻል፣ ለምን ያህል ጊዜ ልጠቀም?
- ይህ እብጠት ስታይ ነው ወይስ ካላዚዮን፣ መወገድ ያስፈልገዋል?
- ትርፍ ሥጋው እይታዬን ሊጎዳ ይችላል? መቼ ነው ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልገው?
- መርገብገቡ የነርቭ ችግር ምልክት ሊሆን ይችላል?
ምንጮች
- NHS. Dry eyes.
- NHS. Stye.
- NHS. Twitching eyes and legs.
- American Academy of Ophthalmology, EyeSmart. Pinguecula and Pterygium.
- American Academy of Ophthalmology, EyeSmart. Retinal Detachment: Symptoms and Warning Signs.
- Mayo Clinic. Dry eyes.
ጥያቄዎችና መልሶች · 12
ዶክተር የኔ ልጂ 8ወሩ ነው እና አይኑ ያለቅሳል እናም እንባው አይናር ይሆናል ። የሆነ ነገር በለኝ please
በዚህ እድሜ እንባና አይናር ብዙ ጊዜ የእንባ ቱቦ ገና ስላልተከፈተ ነው፣ አብዛኛው እስከ አንድ አመት በራሱ ይከፈታል። በፈላና በቀዘቀዘ ውሃ በንፁህ ጥጥ ማፅዳትና የአይኑን ውስጠኛ ጥግ በቀስታ ማሸት ይረዳል። ጥጉ ከቀላና ካበጠ ግን ቶሎ ይታይ።
ሰላም ዶክተር ዓይኔ ላይ liክ እንደ ትርፍ ገላ ያለች ነገር ከስምንት ዓመት በፊት ነበር የወጣችው። ግን እያደገች እንደሆነ ይሰማኛል፣ ሕመም የለውም። ለመseራት ፈልጌ ሌላ ኢንፌክሽን ይፈጠራል ብዬ ፈርቼ እስካሁን አልታየሁትም። ምን ይሻላል? አንተ ጋ መምጣት አልችልም፣ እኔ ማድረግ ያለብኝ ካለ ብትነግረኝ?
ለስምንት ዓመት ህመም ሳይኖረው ቀስ ብሎ የሚያድግ ነገር ብዙ ጊዜ ጉዳት የሌለው ትርፍ ቆዳ ወይም እባጭ ነው። ማስወገዱ ቀላል ነው፣ ቁስሉ ንጹህ ከተያዘ ኢንፌክሽን ብዙም አይከሰትም። እያደገ ስለሆነ ግን በአቅራቢያዎ ያለ የዓይን ሐኪም ይየው፤ ቤት ውስጥ ለመቁረጥ ወይም ለማሰር አይሞክሩ።
እኔ አይኔ ላይ እብጠት አለሁ ከልጅነቴ ጀምሮ እየተቃይረ ያመኛል ህክምና አድርጌ ነበር ብዙ ሰዓት መፍትሄ የለውም ተናነሽ እብጣቶች ናቸው በዓላህ መድሃኒት ካለህ ሶስት ጊዜ ሙሉ ምርመራ ተመርምሬ ነበር
ተደጋግሞ የሚወጣ የአይን ቆብ እብጠት ብዙ ጊዜ በቆቡ ጠርዝ ያሉ ትናንሽ የዘይት ቀዳዳዎች ሲደፈኑ ነው። በቀን ሁለቴ ለ10 ደቂቃ ሞቅ ያለ ጨርቅ አድርገው ቀስ ብለው ማሸት ተደጋጋሚነቱን ይቀንሳል። አንድ ቦታ ላይ ደጋግሞ ከወጣ ግን ናሙና ተወስዶ መመርመር አለበት።
እኔ አይኔን ዳርዳሩን ይበላኛል እና ይቆረቁረኛል ለዚህስ ምን ትላለህ
የሽፋሽፍት ጠርዝ ማሳከክና እንደ አሸዋ መቆርቆር ብዙ ጊዜ ጠርዙ ሲቆጣ ወይም አይን ሲደርቅ ነው። ጠዋትና ማታ ሞቅ ያለ ጨርቅ አድርገው ጠርዙን በንጹህ ውሃ ያጽዱ፣ አይንዎን አያሹ፣ ስልክ ሲያዩም ደጋግመው ያርገብግቡ።
ያለ ዶክተር ትዕዛዝ የዓይን ማለስለሻ ጠብታ ከፋርማሲ ብንገዛ ችግር አለው እንዴ?
ማለስለሻ ጠብታ ማለት ሰው ሰራሽ እንባ ነው፣ ለደረቅ አይን ያለ ትዕዛዝ መጠቀም ችግር የለውም። ስቴሮይድ ወይም አንቲባዮቲክ የያዙትና ቀይነትን ያጠፋሉ የሚባሉት ግን ያለ ሐኪም መወሰድ የለባቸውም።
ማታ ማታ ወይም መሸት ሲል ዓይኔ ድርቅ የማለት ነገር ይሰማኛል፣ ሕመም ሳይሆን ልክ እንቅልፍ እንደመጣበት ሰው። የምን ችግር ነው?
ስክሪን ላይ ረጅም ሰዓት ስንቆይ አይናችን የሚያርገበግበው ስለሚቀንስ እንባው ይተናል፣ ማታ ላይ ድርቀት የሚሰማውም ለዚህ ነው። በየመሃሉ አይንዎን ያሳርፉ፣ ሆን ብለው ያርገበግቡ፣ ከነፋስና ከደረቅ አየር ፊት ለፊት ይራቁ።
የግራ ዐይኔ ያለቅሳል።
አንድ ዓይን ብቻ ከሆነ ብዙ ጊዜ የእንባ መውረጃው በመጥበቡ ነው። በሞቀ ጨርቅ የዓይኑን ውስጠኛ ማዕዘን ቀስ ብለው ይጫኑ። ማሳከክም አብሮት አለው ወይስ እንባ ብቻ?
የአይን መቅላት ምንድነው ሀኪም ስሄድ ጠብታ ብቻ ነው የሚሰጡኝ
መቅላቱ ከከባድ ሕመም፣ ከዕይታ መደብዘዝ ወይም ብርሃን ከማስቸገር ጋር ከመጣ፣ ወይም ሌንስ የሚያደርጉ ከሆነና ዓይንዎ ካመመ በዚያው ቀን መታየት አለበት። ተደጋጋሚ መቅላት ብዙ ጊዜ ከመድረቅ፣ ከአለርጂ ወይም ከአቧራና ከፀሐይ ይመጣል። አንዳንድ ጠብታዎች ከታዘዘው ጊዜ በላይ ሲወሰዱ ራሳቸው መቅላትና ጉዳት ያመጣሉ። ለሳምንታት የሚመላለስ መቅላት ትርፍ ሥጋ ወይም ሌላ ችግር መሆኑን ለማወቅ የዓይን ሐኪም እንዲመረምረው እንመክራለን።
ቀኝ አይኔ ይቀላል፣ ያቃጥለኛል እና እንባ በጣም አለኝ፤ ማሳከክ የለብኝም።
ቀልቶ የሚያቃጥልና እንባ የሚያፈስ ዓይን ብዙ ጊዜ ቫይረስ ወይም አቧራ ነው። አያሹት፣ ቀዝቃዛ ንጹሕ ጨርቅ ይያዙበት። ብርሃን ካስቸገረ፣ እይታ ከደበዘዘ ወይም ሕመሙ ከበረታ በዚያው ቀን ዓይን ሐኪም ይታዩ።
አይን ስር ያለ እብጠት እንዴት ነው ሚጠፋው
ዓይን ዙሪያ ድንገት ካበጠና ከንፈር ወይም ፊትም አብጦ መተንፈስ ከከበደ አሁኑኑ ድንገተኛ ሕክምና ይሂዱ፤ እብጠቱ ከሕመም፣ ከመቅላት፣ ከትኩሳት ወይም ከእይታ ለውጥ ጋር ከሆነ ዛሬውኑ ሐኪም ይዩ። ቀላል እብጠት ብዙ ጊዜ በእንቅልፍ ማጣት፣ በጨው፣ በአለርጂ ወይም በማልቀስ ይመጣል፤ በቂ እንቅልፍ፣ ጨው መቀነስና ቀዝቃዛ ንጹሕ ጨርቅ እንመክራለን። እግርም ካበጠ ወይም ሽንት አረፋ ካበዛ ኩላሊትን ለማረጋገጥ በዚህ ሳምንት ይመርመሩ።
Yena yasakikagnal demo yabixalal.
Masakek ena ebtet abzagnaw gize alerji new. Aynwon ayashu, qezqaza nitsuh chirq le 10 deqiqa aynwo lay yadrgu.
እኔ እንቅልፍ ችግር የለብኝም፣ ቡና እና ሻይም በመጠን ነኝ፣ ስልክም ላይ አልቆይም ያንን ያህል ግን አይኔ ስር እና ላይ በጣም የመንቀጥቀጥ ሁኔታ አለብኝ
ፊትዎ በአንድ በኩል ከወደቀ፣ ከደከመ ወይም ንግግርዎ ከተሳሰረ አሁኑኑ ወደ ኢመርጀንሲ ይሂዱ። ከዚህ ውጭ ከዓይን በላይና በታች ያለ መርገብገብ ብዙ ጊዜ ከድካም፣ ከጭንቀት ወይም ከዓይን መድረቅ ይመጣል፤ በሳምንታት ውስጥም ራሱ ይቆማል። ከሁለት ሳምንት በላይ ከቀጠለ፣ ዓይንዎን ሙሉ በሙሉ ከጨፈነ ወይም ወደ ጉንጭና አፍ ከተዛመተ፣ የነርቭ ችግር አለመሆኑን ለማረጋገጥ በአንድ ሁለት ሳምንት ውስጥ ሐኪም እንዲያይዎ እንመክራለን።
ተያያዥ ርዕሶች
በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው፤ የግል የሕክምና ምክር አይደለም። ድንገተኛ ችግር ካለ 911 (አሜሪካ) ወይም 907 (አዲስ አበባ)።
ሁሉም ጽሑፎች · ስለ እኛ · ያግኙን
ትራኮማን መከላከልና የSAFE ስትራቴጂ
ራስ ምታት
ስሊፕ ፓራሊሲስ (በእንቅልፍ መካከል መንቀሳቀስ አለመቻል)
ቡናና ካፊን በሰውነታችን ውስጥ