ማዲያትና የማንጫ ክሬሞች፦ ፊት ላይ የሚወጣ ጥቁር ነጠብጣብና በውስጣቸው ያለው አደጋ
Dark spots (melasma) and skin-lightening creams
በሐኪም (MD) የተጻፈ · Written by an MD · 2026-09-26
ምንድን ነው?
ቆዳችን ውስጥ ሜላኒንን (melanin) የሚሰሩ ትናንሽ ሴሎች አሉ። ቆዳችንን ቀለም የሚሰጠው ይህ ሜላኒን ነው። ፀሐይ እነዚህን ሴሎች ስትመታቸው፣ ሙቀት ሲበዛ፣ ወይም ሆርሞናችን ሲቀያየር፣ ለምሳሌ በእርግዝና ጊዜ ወይም የወሊድ መከላከያ ኪኒን ሲወሰድ፣ እነዚህ ሴሎች ከመጠን በላይ በጣም ይሰራሉ። ውጤቱ ማዲያት (melasma) ነው፦ ጉንጭ፣ ግንባር፣ ከከንፈር በላይና አፍንጫ ላይ የሚወጣ ቡናማ ወይም ግራጫ ጠፍጣፋ ነጠብጣብ።
ማዲያት ቆሻሻ አይደለም፤ ተላላፊም አይደለም፤ የውስጥ በሽታ ምልክትም አይደለም። በጠቆረ ቆዳ ላይ ይበልጥ የተለመደ ሲሆን፣ ብዙ እህቶቻችንን ከወሊድ በኋላ ይይዛቸዋል።
ችግሩ የሚጀምረው ማዲያቱን «በፍጥነት ለማጥፋት» ስንሞክር ነው። ከአገር ቤት ስም በሌለው ማሰሮ የሚመጡ፣ ወይም በሱቅና በኦንላይን ርካሽ ሆነው የሚሸጡ አንዳንድ የማንጫ ክሬሞች፣ በውስጣቸው ጎጂ ነገሮች አሏቸው።
አደገኛ ምልክቶች
ሜርኩሪ ያለው ክሬም ሲጠቀሙ ከነበረና ከሚከተሉት አንዱ ካለ፣ ሐኪም ያግኙ፦
- እጅ መንቀጥቀጥ፣ መደንዘዝ ወይም በአፍ ዙሪያ መቆጥቆጥ።
- የማስታወስ ችግር፣ ቁጣ ወይም ያልተለመደ ድካም።
- እግር ወይም ፊት ማበጥ፣ የሽንት አረፋ መብዛት (ኩላሊት ፕሮቲን ሲያፈስ ሊታይ ይችላል)።
- የዓይን ወይም የመስማት ለውጥ።
በክሬሞቹ ውስጥ ምን አለ?
- ሜርኩሪ (mercury)፦ የሜላኒንን ፕሮዳክሽን ስለሚያቆም ቆዳን በፍጥነት ያነጣል። ግን በቆዳ አልፎ ወደ ደም ይገባል፤ ኩላሊትንና ነርቭን ይጎዳል። በእርግዝናና በጡት ማጥባት ጊዜ ወደ ልጁም ሊደርስ ይችላል። ክሬሙ በእጅ፣ በትራስ፣ በፎጣና ልጅን በማቀፍ ስለሚተላለፍ፣ ክሬሙን የማይጠቀሙ የቤተሰብ አባላትም በሰውነታቸው ሜርኩሪ ተገኝቶባቸዋል።
- ጠንካራ ስቴሮይድ (strong steroid)፦ ለቆዳ በሽታ በሐኪም የሚታዘዝ ክሬም ነው። ለወራት ፊት ላይ ሲቀባ ቆዳውን ያሳሳዋል፤ ብጉር፣ የሚታዩ የደም ስሮች፣ ስትሬች ማርክ (stretch marks) እና ፈንገስ ያመጣል። ሲቆም ደግሞ ፊቱ ከበፊቱ የባሰ ሊቆጣና ሊጠቁር ይችላል።
- ሀይድሮኪኖን (hydroquinone)፦ በሐኪም ክትትል ለአጭር ጊዜ ሲሰጥ ይረዳል። ያለ ክትትል ለረጅም ጊዜ ሲቀባ ግን ቆዳን ሰማያዊ ጥቁር ሊያደርግ ይችላል (ochronosis)፤ ይህን ለማጥፋት በጣም ከባድ ነው። በአሜሪካ ከ2020 ጀምሮ ያለ ፕሪስክሪፕሽን የሚሸጥ የማንጫ ክሬም ሕጋዊ አይደለም።
ክሬሙን እንዴት ላውቀው?
- ማሸጊያው ላይ ሜርኩሪ (mercury)፣ ካሎሜል (calomel)፣ ሜርኩሪየስ ክሎራይድ (mercurous chloride) ወይም mercurio የሚል ካለ፣ ፈጽሞ አይቀቡት።
- የንጥረ ነገር ዝርዝር ከሌለው፣ ስም በሌለው ማሰሮ ከመጣ፣ ከውጭ አገር በኦንላይን በጣም ርካሽ ከተገዛ፣ ወይም በሳምንታት ውስጥ «ተአምር» ካሳየ ይጠራጠሩ።
- ስም ያለው ማሸጊያም ሙሉ ዋስትና አይደለም። ለመሸጥ ፈቃድ ያለው ምርት መሆኑን ሐኪምዎን ወይም ፋርማሲስቱን ይጠይቁ።
ሲጠቀሙበት ቆይተው ከሆነ
- ሜርኩሪ እንዳለው ከጠረጠሩ ዛሬውኑ ያቁሙ። ማሰሮውን በፕላስቲክ ከረጢት አስረው ያስቀምጡ፤ ቆሻሻ ውስጥ አይጣሉት። እንዴት እንደሚወገድ የአካባቢዎን የጤና ቢሮ ይጠይቁ።
- እጅዎን ይታጠቡ፤ ክሬሙ የነካቸውን ፎጣዎችና የትራስ ልብሶች ያጥቡ።
- ሐኪምዎን የሽንት ሜርኩሪ ቴስት (urine mercury test) ይጠይቁ። ቤት ውስጥ ሌሎች ካሉ፣ በተለይ ልጆችና እርጉዝ ሴቶች፣ እነሱም እንዲመረመሩ ይጠይቁ።
- ስቴሮይድ ክሬም ለወራት ከተቀቡ ግን በድንገት አያቁሙ፤ ሐኪም እንዴት ቀስ ብለው እንደሚቀንሱት ያሳይዎታል።
የማይሰሩ ነገሮች
ሎሚ፣ የጥርስ ሳሙና፣ በረኪና ወይም ሌሎች «የቤት ማንጫዎች» ቆዳውን ያቃጥላሉ። የተቃጠለ ቆዳ ደግሞ ሲድን ይበልጥ ይጠቁራል።
አንገት፣ ብብት ወይም የቆዳ እጥፋት ላይ ወፍራም፣ ቬልቬት የሚመስል ጥቁር ቆዳ (acanthosis nigricans) ካለ፣ የሚያስፈልገው ክሬም ሳይሆን የስኳር ቴስት ነው። ይህ ምልክት ሰውነት ኢንሱሊንን በደንብ እየተጠቀመበት እንዳልሆነ ሊያሳይ ይችላል።
የሚሰራው
- ሰንስክሪን በየቀኑ፦ አዎ፣ ለጠቆረ ቆዳም። በየጠዋቱ ቢያንስ ኤስ ፒ ኤፍ 30 (SPF 30)፣ በተለይ ትንሽ ቀለም ያለው (tinted) ሰንስክሪን ይቀቡ፤ ከቤት ውጭ ከቆዩ ይድገሙ። ኮፍያና ጥላም ይረዳሉ።
- ትዕግስት፦ ውጤቱ በሳምንት ሳይሆን በወራት ነው የሚታየው።
- የቆዳ ሐኪም፦ ሴፍ የሆኑ ክሬሞችን በትክክለኛው መጠንና ጊዜ ያዝልዎታል፤ ክትትልም ያደርጋል።
- ምክንያቱን ማከም፦ ማዲያቱ ከወሊድ በኋላ ከመጣ ብዙ ጊዜ ቀስ ብሎ በራሱ ይቀንሳል። ከወሊድ መከላከያ ኪኒን ጋር ከመጣ ሐኪምዎን ያማክሩ።
ሐኪም መቼ ማየት?
- ሜርኩሪ ያለው ክሬም ተጠቅመው ከሆነ፣ ምልክት ባይኖርም ቴስት ለማድረግ።
- ስቴሮይድ ክሬም ለወራት ፊት ላይ ቀብተው ከሆነ።
- ነጠብጣቡ በፍጥነት ቢያድግ፣ ቅርጹ ወይም ቀለሙ ቢቀያየር፣ ቢደማ ወይም ቢያሳክክ።
- አንገት ወይም ብብት ላይ ወፍራም ጥቁር ቆዳ ካለ።
ለሐኪምዎ የሚጠይቋቸው
- ይህ ማዲያት ነው ወይስ ሌላ የቆዳ ችግር?
- ለቆዳዬ ቀለም የሚሆን ሴፍ ክሬም የቱ ነው፣ ለምን ያህል ጊዜስ?
- የሽንት ሜርኩሪ ቴስት ያስፈልገኛል? ቤተሰቤስ?
- የስኳር ቴስት ማድረግ አለብኝ?
ምንጮች
- U.S. Food and Drug Administration. Mercury Poisoning Linked to Skin Products.
- U.S. Food and Drug Administration. FDA works to protect consumers from potentially harmful OTC skin lightening products (2022).
- U.S. Food and Drug Administration. Skin Facts! What You Need to Know About Skin Lightening Products.
- CDC MMWR 2012;61(2):33-36. Mercury Exposure Among Household Users and Nonusers of Skin-Lightening Creams Produced in Mexico, California and Virginia, 2010.
- Minnesota Department of Health. Skin-lightening products and mercury.
- American Academy of Dermatology. Melasma: diagnosis and treatment; Acanthosis nigricans.
ጥያቄዎችና መልሶች · 7
ትንሽ ማድያት ወቶብኝ ብዙ ክሬም ሞከርኩ አልጠፍ አለኝ ክራሽ እየሰፋ ሔደ
ማዲያት በፀሐይ ብርሃን ይባባሳል፣ ስለዚህ ክሬም ብቻውን አይበቃም። SPF 30 ወይም ከዚያ በላይ የሆነ የፀሐይ መከላከያ በየቀኑ መቀባትና ኮፍያ መጠቀም መሠረቱ ነው። እየሰፋ ከሄደ በቆዳ ሐኪም የሚታዘዙ ክሬሞች አሉ፣ ውጤቱም ከሦስት ወር በኋላ ነው የሚታየው። ምንጫቸው የማይታወቅ ቆዳ የሚያነጡ ክሬሞች ግን ቆዳን ሊጎዱ ይችላሉ።
እኔ ደግሞ ሎሚ እየተጠቀምኩ ነው ያጠቆረብኝ
ሎሚ አሲድ ስለሆነ ቆዳውን ሊያስቆጣ ይችላል፣ የተቆጣ ቆዳ ደግሞ ሲድን የበለጠ ይጠቁራል፣ ፀሐይ ሲያገኘውም ይብሳል። ሎሚውን ማቆም፣ ሽታ የሌለው ሳሙናና ማለስለሻ መጠቀም፣ መላጨትና ማሸትን መቀነስ ይሻላል። ጥቁረቱ ወፍራምና ቬልቬት የሚመስል ሆኖ አንገት ላይም ካለ ከደም ስኳር ጋር ሊያያዝ ስለሚችል ስኳር መመርመር ጥሩ ነው።
ዶክተር ማዲያት አወጣብኝ ከጉንጨ ከፍ ብሎ ከአይኔ ዝቅ ብሎ በሁለቱም ግድም ምን ማድረግ አለብኝ??
በጉንጭ ላይ የሚወጣው ጠቆር ያለ ነገር ከፀሐይና ከሆርሞን ጋር ይያያዛል። ዋናው መፍትሄው ፀሐይን መከላከል ነው፣ በየቀኑ ሰንስክሪን ተቀቡ። ሎሚና ስክራብ ግን ያባብሱታል። መጥፋቱ ወራት ስለሚወስድ አትቸኩሉ።
የእኔ ማዲያት ግዜ እየለየ ይወጣል አንዳንዴ ፊቴ ጥርት ይላል አንዳንዴ ደግሞ ማዲያቴ ግልብጥ ይላል ?
ማዲያት በፀሐይና በሙቀት ይጠቁራል፣ ፀሐይ ሲቀንስ ደግሞ ይጠራል፤ ስለዚህ እየተለዋወጠ መምጣቱ የተለመደ ነው። ደመናማ ቀንም ቢሆን በየቀኑ የፀሐይ መከላከያ ከተቀቡ ልዩነቱ ይታያል።
ማድያት አልጠፉም አለኝ።
ማድያት በፀሐይ በጣም ይነሳል፤ ዋናው መፍትሄ በየቀኑ ጠዋት የፀሐይ መከላከያ ክሬም መቀባትና ኮፍያ ማድረግ ነው። ፊትን ማሸትና የሚያቃጥል ነገር መቀባት ያባብሰዋል፣ ለውጡም ወራት ይወስዳል።
ፊቴን ብቻ ነው የምቀባው። ፀሐይ ጭራሽ አያገኘኝም፣ ቤት ውስጥ ነው የምውለው፤ ግን ምግብ ስሰራ ሙቀት ስለሚያገኘኝ እቀባለሁ። ይህ እንዴት ይታያል?
ቤት ውስጥ ብቻ ለሚውል ሰው ፊትን ብቻ መቀባት በቂ ነው። የምድጃን ሙቀት ግን የፀሐይ መከላከያ አይከላከልም፤ ሲያበስሉ ፊትዎን ከእሳቱና ከእንፋሎቱ ትንሽ ያርቁ።
ፊቴ ብጉር ይወጣና ሲጠፉ ይጠቁራል፤ የፀሀይ መከላከያና ሳሙና ቅባት አሳየኝ
ብጉር ሲጠፋ የሚተወው ጥቁር ምልክት ብዙ ጊዜ ጠባሳ ሳይሆን ቆዳው ከተቆጣ በኋላ የሚቀር ጥቁረት ነው፤ ለመልቀቅ ከወራት እስከ ከአንድ ዓመት በላይ ሊወስድ ይችላል። በየጠዋቱ ቢያንስ ሰላሳ ደረጃ ያለው የፀሐይ መከላከያ፣ ለስላሳ ሳሙናና ቀዳዳ የማይደፍን ቅባት እንመክራለን፤ መጨመቅ፣ ሎሚና ስም የሌለው የማንጫ ክሬም ግን ያባብሱታል። ብጉሩ ከበዛ፣ ጥልቅና የሚያም ከሆነ ወይም ጉድጓድ ጠባሳ ከተወ፣ ብጉሩን የሚያስቆምና ምልክቱን የሚያቀል ሕክምና እንዲያዝልዎ በሚቀጥሉት ሳምንታት የቆዳ ሐኪም ያማክሩ።
ተያያዥ ርዕሶች
በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው፤ የግል የሕክምና ምክር አይደለም። ድንገተኛ ችግር ካለ 911 (አሜሪካ) ወይም 907 (አዲስ አበባ)።
ሁሉም ጽሑፎች · ስለ እኛ · ያግኙን
የቆዳ አለርጂ
ኮላጅን ዱቄት ወይስ ምግብ፦ ለቆዳ ምን ይረዳል?
ቅድመ ስኳር በሽታ