ፔይንኪለር፦ ሦስት ስህተቶችን ያስወግዱ
Painkiller safety: NSAIDs, dehydration and duplicate ingredients
ጽሑፍ፦ ሕክምና · Prepared by Hikimna · 2026-10-31
የተለያዩ ስሞች፣ አንድ ቤተሰብ
ለጀርባ ሕመም ዲክሎፌናክ፣ ከዚያ ለራስ ምታት ኢቡፕሮፌን ወሰዱ? ስማቸው ቢለያይም፣ የሚመጡት ከአንድ የመድኃኒት ቤተሰብ ነው። እነዚህን መደራረብ፣ ለኩላሊትና ለሆድ ጉዳት ሊያጋልጥ ይችላል።
ስለሚዋጡ መድኃኒቶች
ናፕሮክሰንም የዚሁ ቡድን ነው። ኤንሴድስ ይባላሉ። እዚህ የምናወራው ስለሚዋጡት መድኃኒቶች ነው። በአግባቡ ሲወሰዱ ሕመምንና ኢንፍላሜሽንን ይቀንሳሉ። ግን እነዚህን ሶስት ስህተቶች አስተውሉ።
አንደኛ፦ መድኃኒቶችን መደራረብ
አንደኛ፦ ስማቸው ስለተለያየ አብሮ መውሰድ። ዲክሎፌናክን፣ ኢቡፕሮፌንን ወይም ናፕሮክሰንን ያለ ሕክምና ምክር አያጣምሩ። አንዳንድ የጉንፋን መድኃኒቶችም የእነዚህ መድኃኒቶች ንጥረ ነገር ሊኖራቸው ይችላል። በቦክሱ ላይ ያለውን አክቲቭ ኢንግሪዲየንት፣ ዋናውን የመድኃኒት ንጥረ ነገር፣ ይመልከቱ።
ሁለተኛ፦ ሰውነት ውሃ ሲያጣ
ሁለተኛ፦ ዲሃይድሬሽን እያለ ፔይንኪለር መውሰድ። በተቅማጥ፣ በትውከት ወይም በቂ ፈሳሽ ባለመውሰድ ሰውነትዎ ውሃ ሲያጣ፣ ወደ ኩላሊት የሚደርሰው ደም ሊቀንስ ይችላል። እነዚህን ፔይንኪለሮች መውሰድ፣ ድንገተኛ የኩላሊት ጉዳት ሊያመጣ ይችላል። ከመውሰድዎ በፊት ምክር ይጠይቁ።
ሦስተኛ፦ ደጋግሞ በራስ መቀጠል
ሶስተኛ፦ ሕመሙ በተመለሰ ቁጥር፣ እንዳሻዎት መቀጠል። የኩላሊት ችግር፣ ስኳር ወይም ደም ግፊት ካለዎት፣ ወይም አንዳንድ የደም ግፊትና ሽንት የሚያበዙ መድኃኒቶችን የሚወስዱ ከሆነ፣ ሪስኩ ሊጨምር ይችላል። ለፋርማሲስትዎ ሙሉ የመድኃኒት ዝርዝርዎን ያሳዩ። የታዘዘልዎትን መድኃኒት ግን በራስዎ አያቋርጡ።
ፓራሲታሞልና ጉበት
ፓራሲታሞል፣ ወይም አሴታሚኖፌን፣ የዚህ ቡድን አይደለም። ግን ከተፈቀደው መጠን በላይ መውሰድ፣ ጉበትዎን በከባድ ሁኔታ ሊጎዳ ይችላል። ጉበት ፓራሲታሞልን ሲያቀናብር፣ ትንሽ መርዛማ ንጥረ ነገር ይፈጠራል። መጠኑ ሲበዛ፣ ሰውነት ይህን ማስወገድ ያቅተውና መርዙ ጉበትዎን ሊጎዳ ይችላል። በሁለት የተለያዩ የጉንፋንና የሕመም መድኃኒቶች ውስጥ ተመሳሳይ ንጥረ ነገር እንዳልተደገመ ይፈትሹ። ምልክቶች ዘግይተው ሊታዩ ይችላሉና፣ ከተፈቀደው በላይ ከወሰዱ፣ ምልክት ባይኖርም ወዲያውኑ የሕክምና እርዳታ ይጠይቁ።
አስቸኳይ ምልክቶች
ሽንትዎ በጣም ከቀነሰ፣ ጥቁርና እንደ ሬንጅ የሚጣበቅ ሰገራ ካዩ፣ ወይም ደም ካስታወኩ፣ አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ይፈልጉ።
ንጥረ ነገሩን ይወቁ
እዚህ ላይ፣ አንድ ታብሌት ወሰዱ ማለት፣ ኩላሊትዎ ተጎዳ ማለት አይደለም። ሪስኩ በመጠን፣ በቆይታና በጤናዎ ሁኔታ ይለያያል። ዛሬ የቤትዎን መድኃኒቶች ይመልከቱ። ስማቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ውስጣቸው ያለውንም ይወቁ።
ምንጮች
ምንጮች
- https://www.niddk.nih.gov/health-information/kidney-disease/keeping-kidneys-safe
- https://www.nhs.uk/medicines/diclofenac/taking-diclofenac-with-other-medicines-and-herbal-supplements/
- https://www.nhs.uk/medicines/paracetamol-for-adults/
- https://www.fda.gov/consumers/consumer-updates/dont-overuse-acetaminophen
ጥያቄዎችና መልሶች
የመጀመሪያውን ጥያቄ ይጠይቁ።
ተያያዥ ርዕሶች
ለትምህርት ብቻ ነው፤ የግል የሕክምና ምክር አይደለም። ድንገተኛ ችግር ካለ 911 (አሜሪካ) ወይም 907 (አዲስ አበባ)።
ሁሉም ጽሑፎች · ስለ እኛ · ያግኙን
ሥር የሰደደ የኩላሊት በሽታ፣ አደጋ ምክንያቶችና ቅድመ ምርመራ
የባህል ሕክምናና የሐኪም መድኃኒትዎ