ሕክምናHikimna · Amharic health reference
በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው። Written by an MD. Educational only.
12

የጆሮ ሰም

Earwax

በሐኪም (MD) የተጻፈ · Written by an MD · 2026-09-20

ምንድን ነው?

የጆሮ ሰም (earwax) ቆሻሻ ብቻ አይደለም። በጆሮ ቦይ (ear canal) ውስጥ የሚፈጠር ተፈጥሯዊ መከላከያ ነው። አቧራንና ትንንሽ ቅንጣቶችን ይይዛል፣ ቆዳው እንዳይደርቅ ይረዳል፣ አንዳንድ ተሕዋስያን እንዳይበዙም ያግዛል። ስለዚህ ትንሽ ሰም መኖሩ መደበኛና ጠቃሚ ነው።

ቀለሙና ጥንካሬው ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። ቢጫ፣ ቡናማ፣ ለስላሳ ወይም ደረቅ መሆኑ ብቻውን በሽታ አይደለም። ብዙ ጊዜ ጆሮ ራሱን ያጸዳል። ስንናገርና ምግብ ስናኝክ የመንጋጋችን እንቅስቃሴ የድሮውን ሰም ቀስ በቀስ ወደ ውጭ ያጓጉዛል፤ ወደ መክፈቻው ሲደርስ ደርቆ በራሱ ይወጣል።

ችግሩ የሚጀምረው ሰሙ ብዙ ሆኖ የጆሮ ቦዩን ሲዘጋ ነው። በእኛ ማኅበረሰብ ጆሮን በጥጥ ዘንግ (cotton swab)፣ በክብሪት ወይም በሌላ ዕቃ መቆርቆር የተለመደ ነው። ይህ ግን ሰሙን ከማውጣት ይልቅ ወደ ውስጥ ይገፋዋል። መዘጋቱ ብዙ ጊዜ ከንጽሕና እጥረት ጋር አይያያዝም።

አደገኛ ምልክቶች

ከሚከተሉት አንዱ ካለ ወዲያውኑ እርዳታ ይፈልጉ፦

  • ከባድ የጆሮ ሕመም።
  • ከጆሮ ደም ወይም መግል የሚመስል ፈሳሽ መውጣት።
  • ትኩሳት ከጆሮ ሕመም ጋር።
  • ድንገተኛ የመስማት መቀነስ።
  • ከባድ ማዞር።
  • ዕቃ ወደ ጆሮ ከገባ። በራስዎ ለማውጣት አይሞክሩ።
  • በክሊኒክ የሰም ማስወገድ ሂደት ሕመም ወይም ማዞር ካመጣ፣ ወዲያውኑ ለባለሙያው ይንገሩ።

ቤት ውስጥ ምን ማድረግ?

  • የውጭውን ጆሮ ብቻ በለስላሳ ጨርቅ ይጥረጉ። ጨርቁን ወደ ውስጥ አይግፉ።
  • ጥጥ ዘንግ፣ ሹካ፣ ክብሪት ወይም ሌላ ማንኛውንም ዕቃ ወደ ጆሮ ውስጥ ፈጽሞ አያስገቡ። ሰሙን ወደ ውስጥ ይገፋሉ፣ የጆሮ ቦዩን ይቧጫሉ፣ ታምቡሩንም ሊቀዱ ይችላሉ። ትንሽ ቁስል ከተፈጠረ ባክቴሪያ ወይም ፈንገስ ሊበዛ ይችላል።
  • ከመታጠብ በኋላ የውጭውን ጆሮ በቀስታ ያድርቁ፤ ውሃ ለማውጣት በጆሮ ውስጥ አይቆፍሩ።
  • የጆሮ ሻማ (ear candling) አይጠቀሙ። ደህንነቱና ጥቅሙ ያልተረጋገጠ ነው፤ ቃጠሎ፣ ተጨማሪ መዘጋት ወይም የታምቡር ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።
  • ጆሮ ውስጥ ያለውን ነገር ባለሙያ ሳያይ በኃይል ማጠብ አደገኛ ነው። የተዘጋ ጆሮ ፈጣን መፍትሔ ይፈልጋል ብለው አይቸኩሉ።
  • ጆሮን በብዛት ማጽዳት እንኳን ቆዳውን ያበሳጫል፣ መከላከያውንም ያሳንሳል። በየቀኑ መቆፈር የመዘጋት እድልን ይጨምራል እንጂ አይቀንስም።
  • ቀላል የሰም መዘጋት መሆኑና ታምቡሩ ጤናማ መሆኑ በባለሙያ ከታወቀ፣ ሰሙን የሚያለሰልስ ጠብታ ሊመከር ይችላል። ጠብታውን እንደ መመሪያው ብቻ ይጠቀሙ፤ የተመከረውን ቀንና መጠን አይበልጡ። በፋርማሲ የሚገኝ ማለስለሻ ሁሉ ለሁሉም ሰው ተስማሚ አይደለም።
  • ታምቡር ተቀዶ ሊሆን ከቻለ፣ በቅርቡ የጆሮ ቀዶ ሕክምና ካደረጉ፣ በጆሮ ውስጥ ቱቦ ካለ ወይም ፈሳሽ ካለ፣ በራስዎ ጠብታ ወይም ውሃ አይጠቀሙ።
  • የስኳር በሽታ ወይም የበሽታ መከላከያ አቅም ችግር ካለብዎ፣ ወይም ለልጅ ከሆነ፣ ማንኛውንም ነገር ከመጀመርዎ በፊት ምክር ይጠይቁ።
  • የመስሚያ መሣሪያ የሚጠቀሙ ከሆነ መሣሪያውን እንደ መመሪያው ያጽዱ።
ምልክቶች

የጆሮ ሰም ሲዘጋ፦

  • መስማት መደብዘዝ።
  • ጆሮው እንደተሞላ መሰማት።
  • ማሳከክ ወይም ሕመም።
  • በጆሮ ውስጥ የሚጮኽ ወይም የሚያቃጭል ድምፅ።
  • አልፎ አልፎ ሳል ወይም ማዞር።

እነዚህ ምልክቶች በጆሮ ሰም ብቻ አይመጡም። የጆሮ ኢንፌክሽን፣ የታምቡር (eardrum) ጉዳት ወይም ሌላ የመስማት ችግር ተመሳሳይ ስሜት ሊያመጣ ይችላል። ስለዚህ በግምት ከመታከም ይልቅ ጆሮውን በባለሙያ ማስመርመር ይሻላል።

ለመዘጋት የበለጠ ተጋላጭ የሆኑት፦ በተፈጥሮ ብዙ ወይም ደረቅ ሰም የሚያመነጩ፣ ጠባብ ወይም ጠመዝማዛ የጆሮ ቦይ ያላቸው፣ በዕድሜ የገፉ፣ የመስሚያ መሣሪያ (hearing aid) ወይም የጆሮ ማዳመጫ በብዛት የሚጠቀሙ፣ የቆዳ ችግር ያለባቸው፣ በጆሮ ቦይ ውስጥ ብዙ ጸጉር ያላቸው፣ ወይም ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ መዘጋት ያጋጠማቸው ሰዎች ናቸው።

ሐኪም መቼ ማየት?
  • መስማት ከደበዘዘ፣ ጆሮ እንደተሞላ ከተሰማ፣ ማሳከክ፣ ሕመም ወይም የሚያቃጭል ድምፅ ካለ።
  • በልጅ ላይ የመስማት መደብዘዝ ከታየ አይዘግዩ። ንግግርን፣ ትምህርትንና ትኩረትን ሊነካ ይችላል።
  • አዋቂ ሰው ቴሌቪዥንን ከፍ ሲያደርግ፣ ደጋግሞ "እንደገና በል" ሲል ወይም በስልክ መስማት ሲከብደው።
  • ሰሙ ከተወገደ በኋላ ምልክቱ ካልተሻለ። ሌላ ምክንያት መፈለግ ያስፈልጋል።
  • መዘጋቱ ተደጋጋሚ ከሆነ፣ መደበኛ ምርመራ ለማቀድ።
  • የመስሚያ መሣሪያ የሚጠቀሙ ከሆነ ጆሮዎን በየጊዜው ያስመርምሩ።

በክሊኒክ የጤና ባለሙያው በጆሮ መመልከቻ ውስጡን በጥንቃቄ ያያል። ችግሩ ሰም ከሆነ እንደ ሁኔታው በማለስለሻ ጠብታ፣ በቀስታ በሚደረግ ማጠብ፣ በመሳብ ወይም በትንሽ መሣሪያ ያስወግደዋል። ዘዴው የሚመረጠው ታምቡሩ፣ የጆሮ ቦዩና የጤናዎ ሁኔታ ከታየ በኋላ ነው። ጠንካራ ሰም ለማስወገድ አንዳንድ ጊዜ ከአንድ ጊዜ በላይ ጉብኝት ያስፈልጋል።

መከላከያ
  • ጆሮዎን በየቀኑ አይቆፍሩ። የውጭውን ጆሮ ብቻ በለስላሳ ጨርቅ ያጽዱ።
  • ወደ ጆሮ ውስጥ ምንም ነገር አያስገቡ። ጥጥ ዘንግ ለውጭው ጆሮ ብቻ ነው።
  • የመስሚያ መሣሪያ፣ የጆሮ ማዳመጫ ወይም የጆሮ መዝጊያ ለረጅም ሰዓት ከሚጠቀሙ ጆሮዎ እረፍት ይስጡ፤ መሣሪያውን በንጽሕና ይያዙ።
  • በተደጋጋሚ የሚዋኙ ከሆነ ስለ ጆሮ ደረቅነትና መከላከያ ከባለሙያ ጋር ይወያዩ።
  • መዘጋቱ ተደጋጋሚ ከሆነ መቼ መመርመር እንዳለብዎ ከባለሙያዎ ጋር እቅድ ያውጡ።
ለሐኪምዎ የሚጠይቋቸው
  • ጆሮዬ በሰም ተዘግቷል ወይስ ሌላ ችግር አለ?
  • ማለስለሻ ጠብታ መጠቀም እችላለሁ? የትኛውን፣ ለምን ያህል ቀን?
  • መዘጋቱ ተደጋጋሚ ስለሆነ በምን ያህል ጊዜ ልመርመር?
  • የመስሚያ መሣሪያዬን እንዴት ላጽዳ?
ምንጮች

ጥያቄዎችና መልሶች · 12

nets

ዶ/ር እባክህ እርዳኝ አፍጫዬ በጣም ይታፈናል በጣም ፈሳሽ አለው በጣም ያስነጥሰኛል እና እንዳልጮህ ሰው እንዳልረብሽ ብዬ አፍነዋለው እና አሁን ወር አለፈኝ ቀኝ ጆሮዬ መስማት አቆመ መዳኒት ተሰቶኝ ነበረ ግን ለውጥ አላገኘሁም አሁን ቀኙም መስማት እየቀነሰ ነው ምን ላድርግ እባክህ እርዳኝ

ሕክምና

ለአንድ ወር የቆየ የመስማት መቀነስ በመድኃኒት ካልተሻለና ሌላውም ጆሮ እየቀነሰ ከሆነ፣ ጆሮው ተመርምሮ የመስማት ምርመራ መደረግ አለበት፤ በዚህ ሳምንት ቢሆን ይሻላል። እስከዚያ ሲያስነጥስዎ አፍንጫዎን አያፍኑ።

user18

እረ ዶክተር በናትህ መልስልኝ ከአፍጫየ መጥፎ ጠረን ይወጣል ምንላድርግ

ሕክምና

ሽታው ከአንድ በኩል ብቻ ነው ወይስ ከሁለቱም? ለጊዜው በቀን ሁለቴ አፍንጫዎን በጨው ውሃ ያጥቡ፤ ብዙ ጊዜ ከሳይነስ ወይም ከደረቀ ንፍጥ ይመጣል። ከአንድ በኩል ብቻ ከሆነና ከሳምንታት በላይ ከቆየ አፍንጫው መታየት አለበት።

ab03

በማርያም Dr መፍትሄ ንገረኝ ከልጅነቴ ጀምሮ ጆሮዬ ቢጫ የቀላቀለ ፈሳሽ አለው ከዚህ በፊት ህክምና ተደርጎልኝ መድሃኒት ሰተዉኝ ነበረ የተወሰነ ጊዜ ፈሳሹ ቆሞ ከዛ ይመለሳል እባክህ እርዳኝ እባክህ ንገረኝ ምን እንደሚሆን በማርያም ዶ/ር

ሕክምና

ከልጅነት የቆየና በመድሀኒት ቆሞ የሚመለስ የጆሮ ፈሳሽ ብዙ ጊዜ የጆሮ ታምቡር ተቀዶ የቆየ ኢንፌክሽን ስላለ ነው። መድሀኒት ለጊዜው ብቻ ያቆመዋል፣ ዘላቂው መፍትሄ ሀኪም አይቶ ታምቡሩን በቀዶ ጥገና መዝጋት ነው። እስከዚያው ውሃ እንዳይገባ ይጠንቀቁ።

kadi

Dr. Joro cohat mate?

ሕክምና

Joro chuhet bezu gize ke tilik dimts, ke joro kuk wey ke dem gifit gar yiyayazal. Band joro bicha new wey be hulet? Iskezaw joron be inchet atkoskosu, tilik dimtsim yiraku.

blac

ዶ/ር በናትህ መልስልኝ ቀኝ ጆሮዬን እንጨት ወጋኝ እና አየር እየወጣ ነው ምን ማድረግ አለብኝ

ሕክምና

አየር የሚወጣ ከመሰለዎት የጆሮ ታምቡር ተቀዶ ሊሆን ይችላል። ውሃ እንዳይገባ ይጠብቁ፣ ጠብታም ሆነ ምንም ነገር አያስገቡ፣ አፍንጫን በሃይል አይናፍጡ። ብዙ ጊዜ በራሱ ይድናል፤ መግል፣ ከባድ ህመም፣ ማዞር ወይም የመስማት መቀነስ ካለ ግን የጆሮ ሀኪም ቶሎ ይዩ።

goja

አንድ ጆሮዬ እየተዘጋ አስቸገረኝ ግን አያመኝም፣ በተለይ ሻወር ስወስድና ስተኛ ጥቅጥቅ ይላል

ሕክምና

ሳያም ውሃ ከነካው በኋላ የሚብስ መደፈን ብዙ ጊዜ የተከማቸ የጆሮ ሰም ነው፤ ውሃ ሲገባበት ያብጣል። በጥጥ ከመጎርጎር ይልቅ ለጥቂት ቀናት ለብ ያለ የወይራ ዘይት ጠብታ ማድረግ ያለሰልሰዋል። ካልለቀቀ ግን በጤና ተቋም በቀላሉ ይታጠባል።

edas

ጆሮዬ በልጅነቴ ጀምሮ ይመግላል፣ በአንዱ ጆሮዬ አይሰማኝም፣ መግል ቀን በቀን ነው የማወጣው። ለዚህ መፍትሔ ይኖራል?

ሕክምና

አዎ፣ መፍትሄ አለው። ከልጅነት ጀምሮ መግል የሚወጣና የማይሰማ ጆሮ ብዙ ጊዜ የታምቡር መቀደድ ነው። ኢንፌክሽኑን አድርቆ ቀዳዳውን በቀዶ ጥገና መጠገን ይቻላል፣ መስማትም ሊሻሻል ይችላል፤ ስለዚህ በጆሮ ሐኪም መታየት ያስፈልጋል። እስከዚያው ውሃ እንዳይገባበት ይጠንቀቁ።

elha

አንደኛው ጆሮዬ በማጽጃው ካጸዳሁት በኋላ መስማት ካቆመ ቆየ። ምን ሊሆን ይችላል?

ሕክምና

ብዙ ጊዜ በማፅጃው ሰሙ ወደ ውስጥ ተገፍቶ ታምቡሩ ላይ ተጣብቆ ነው፤ አንዳንዴ ደግሞ ታምቡሩ ራሱ ተጎድቶ ሊሆን ይችላል። ከእንግዲህ ምንም ነገር አያስገቡ። ሰም ከሆነ ታጥቦ ወዲያው ይመለሳል፣ ስለዚህ ጆሮዎ ቢታይ ይሻላል።

hamz

ጆሮዬ ውስጥ ቫይብሬት ያደርጋል፤ ምንድነው? እንዲያ ሲያደርግ ምን ይደረጋል?

ሕክምና

ጆሮ ውስጥ እንደ ንዝረት ወይም እንደ ክንፍ ምት የሚሰማ ስሜት ብዙ ጊዜ ከጆሮ ታምቡር ጀርባ ያሉ ትናንሽ ጡንቻዎች ሲንቀጠቀጡ ነው። አደገኛ አይደለም፤ ድካም፣ ጭንቀትና ብዙ ቡና ያባብሱታል። ከጉንፋን ወይም ከአለርጂ በኋላ ጆሮ ከተደፈነ ግን የጆሮ አየር መንገድ መዘጋት ነው፤ ማዛጋት፣ ማኘክና አፍንጫን ይዞ በቀስታ መንፋት ይከፍተዋል። ከሳምንት በላይ ከቀጠለ ወይም መስማት ከቀነሰ መመርመር ያስፈልጋል።

mart

ጆሮዬ በጣም ነው የሚያመኝ፣ ኢርፎን ሳደርግ ችግር አለው?

ሕክምና

ድምፁን ከፍ አድርገው ረጅም ሰዓት ማዳመጥ ጆሮን ያማል። ድምፁን ዝቅ አድርገው በየሰዓቱ አረፍ ያድርጉ፣ ኢርፎኑንም ንጹህ ያድርጉ። ጆሮ ውስጥ ጠልቆ የሚገባው አይነት ከሆነም ቀይረው ይሞክሩ።

kidi

ጆሮየን በጣም ያመኛል

ሕክምና

ፈሳሽ ይወጣል ወይስ ህመሙ ብቻ ነው? ፈሳሽ ወይም ትኩሳት ካለ ኢንፌክሽን ስለሚሆን መድሀኒት ያስፈልገዋል። ህመሙ ብቻ ከሆነ ጆሮ ውስጥ ምንም አያስገቡ፣ ለብ ያለ ጨርቅ ማድረግና ጠንካራ ነገር ማኘክን መቀነስ ያስታግሰዋል።

ከቲክቶክ የመጣ ጥያቄ

ጆሮዬን በጣም ያሳክከኛል ማስታገሻ የሆኑ ጠብታ ብወስድስ ችግር አለው

ሕክምና

የጆሮ ማሳከክ ብዙ ጊዜ የጆሮ ቆዳ መድረቅ ወይም በጥጥ፣ በቁልፍና በጣት መፈተግ የሚያመጣው ነው፤ በፈተጋችሁ ቁጥር ይበልጥ ያሳክካል። ምንም ነገር ወደ ጆሮ አታስገቡ። ሕመም፣ ፈሳሽ ወይም የመስማት መቀነስ ካለ ግን የጆሮ ታምቡር ሳይታይ ጠብታ ማድረግ ሊጎዳ ስለሚችል መጀመሪያ ጆሮው መታየት አለበት።

ጥያቄዎ ከታየ በኋላ እዚህ ይወጣል። · Your question appears after it is checked.

ተያያዥ ርዕሶች

በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው፤ የግል የሕክምና ምክር አይደለም። ድንገተኛ ችግር ካለ 911 (አሜሪካ) ወይም 907 (አዲስ አበባ)።
ሁሉም ጽሑፎች · ስለ እኛ · ያግኙን